ፕሬዚዳንት ማክሮን የሩሲያን የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የኮቪድ-19 ምርመራ በሩስያ እንዲደረግረላቸው በሚጠየቁበት ወቅት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ክሬምሊን አረጋግጧል።

የኮቪድ-19 ምርመራው ተቀባይነት የሌለውና ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት መርሃ ግብር ጋር የማይጣጣም ስለሆነ ነው ፈቃደኛ ያልሆኑት ሲል የፈረንሳይ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን ሩሲያውያን ዲኤንኤያቸውን (ዘረ መላቸውን) ሊወስዱ ይችላሉ በሚል ፍራቻ የኮቪድ- 19 ፒሲአር ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም የሚሉም ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች አካላዊ ርቀት የጠበቀ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ውይይት ላይ ሌሎች መሪዎች እንደሚያደርጉት አልተጨባበጡም በመሃከላቸው አራት ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ጠረጴዛ ጫፍና ጫፍ ነው የተቀመጡት።

ይህንንም ያዩ ታዛቢዎች ፕሬዚዳንት ፑቲን ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ለማስተላላፍ ተጠቅመውበታል እያሉ ነው።

ነገር ግን የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት ፕሬዚዳንት ማክሮን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ተቀራርቦ ለመወያየት የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ወይም ጠበቅ ያለ አካላዊ ርቀትን እንዲያከብሩ አማራጮች ቀርበውላቸዋል።

"እጅ መጨባበጥ እንደማይኖር እና ረጅም ጠረጴዛ እንደሚኖር ተረድተናል። ነገር ግን ሩሲያውያን የፕሬዚዳንቱ ዲኤንኤ (ዘረ መል) መውሰዳቸውን መቀበል አልቻልንም" ሲሉ ከምንጮቹ አንዱ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

እኚሁ ምንጭ የሩስያ የስለላ አገልግሎት የፕሬዚዳንት ማክሮን ዲኤንኤ (ዘረ መል) እንዴት እንደሚጠቀምበት አላብራሩም።

"የጤና ፕሮቶኮልን ባላሟላ መልኩ ተመርምረው ምንም አይነት አካላዊ ርቀቶች ሳይጠበቅ ውይይቱ እንዲካሄድ ነው የተጠየቀው፤ ይህ በኛ ተቀባይነት የሌለውና ከፕሬዚዳንቱ የጊዜ ሰሌዳም ጋር የማይጠጣጣም ነው" በማለት የኤሊሴ ቤተመንግስት ምንጭ ለቢቢሲ ገልጿል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን የሩሲያን የኮቪድ-19 ምርመራ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከሩሲያው መሪ ርቀው ውይይት መካሄዱን ክሬምሊን አረጋግጧል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት ሩሲያ የፈረንሳይን አቋም የተረዳች ሲሆን በውይይቶቹ ላይ ምንም ተጽእኖ አላመጣም።

ማክሮን ከፈረንሳይ ከመውጣታቸው በፊት የኮቪድ- 19 ምርመራ ማድረጋቸውን እና ሞስኮ የነበሩት ዶክተራቸውም የአንቲጂን ምርመራ እንዳካሄዱላቸው ሌላ የፈረንሳይ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሮይተርስ ተናግሯል።