ቀጥታ, የአሜሪካ ባሕር ኃይል የኢራን ጦር መርከብን በሚሳዔል መትቶ ሲያሰምጥ ቢያንስ የ80 ሰዎች ሕይወት አለፈ

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት የአሜሪካ ጦር ኃይል በሕንድ ውቅያኖስ ላይ አንድ “የኢራን የጦር መርከብ” በውሃ ውስጥ የሚምዘገዘግ ሚሳዔል በመጠቀም ማስመጡን ተናግረዋል። በኢራን የጦር መርከብ ላይ የነበሩ 80 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ደግሞ የሲሪላንካ መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ማርሻል ሳምፓዝ ቱያኮንታ ለቢቢሲ ሲንሃላ ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአሜሪካ ጥቃት ደርሶባት ከሰመጠችው የኢራን የጦር መርከብ የ80 ሰዎች አስከሬን መገኘቱ ተገለፀ

    በኢራን የጦር መርከብ ላይ የነበሩ 80 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የሲሪላንካ መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ማርሻል ሳምፓዝ ቱያኮንታ ለቢቢሲ ሲንሃላ ተናገሩ።

    የኢራን የጦር መርከብ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሰመጠችው ከአሜሪካ ጦር በደረሰባት ጥቃት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ተናግረዋል።

    የሲሪላንካ ምክትው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሕንድ ውቅያኖስ ጥቃት የደረሰባት መርከብ ላይ የነበሩ ቢያንስ 80 ሰዎች መሞታቸውን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የሲሪላንካ ባሕር ኃይል ቃል አቀባይ ሰነዶች እነደሚያሳዩት 180 ሰዎች በመርከቧ ላይ ነበሩ ብለዋል።

    የሲሪላንካ ባሕር ኃይል ቀደም ሲል ከኢራን የጦር መርከብ የድረሱልኝ ጥሪ ተቀብሎ የ32 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ መቻሉን ተናግሯል።

  2. “ኢራን የበለጠ እና ግዙፍ የጥቃት ማዕበል እየመጣባት ነው” - አሜሪካ

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት እና የጦር ኃይሎች የጋራ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ዳን ኬይን በኢራን ላይ እየተካሄደ ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ ቨርጂኒያ ከሚገኘው የፔንታጎን ዋና ጽህፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

    • የመከላከያ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጦር ኃይል በሕንድ ውቅያኖስ ላይ አንድ “የኢራን የጦር መርከብ” በውሃ ውስጥ የሚምዘገዘግ ሚሳዔል በመጠቀም ማስመጡን ተናግረዋል።
    • የኢራን መንግሥት “ተሸንፏል” ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ “በማያጠራጥር ሁኔታ፣ ያለርህራሄ፣ ከባድ ጉዳት በማድረስ እያሸነፈች ነው” ብለዋል።
    • ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ እንደሚወሰድ ጠቅሰው፤ “የበለጠ እና ግዙፍ የጥቃት ማዕበል እየመጣ ነው” ብለዋል።
    • የአሜሪካ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ዳን ኬን በበኩላቸው የሠራዊቱ ጥቃት “ወደ ምድር እየተስፋፋ ወደ ኢራን ግዛት ጠልቆ እየገባ ነው” ሲሉ ጥቃቱ መጠናከሩን አመልክተዋል።
    • የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ኢራን ፕሬዝዳንት ትራምፕን “ለመግደል” ሞክራለች በማለት ከስሰው፤ ነገር ግን አሜሪካ “ለመግደል ሙከራውን ያደረገውን ቡድን መሪ አድና ገድላለች” ብለዋል።
    • ኢራን ውስጥ 150 በላይ ሰዎች የተገደሉበት በሴቶች ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ተጠይቀው የመከላከያ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ “ምርመራ” እያደረገች ነው ሲሉ መልሰዋል። ነገር ግን ጥቃቱ በእስራኤል ወይስ በአሜሪካ መፈጸሙን እንዲያረጋግጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።
  3. በአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ግድያ ተቃውሞ ያሰሙ የአፍሪካ አገራት

    አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተከትሎ የአፍሪካ አገራት የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል።

    መንግሥታት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እና ሌሎችም ከኢራን ጋር ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ያላቸው ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

    ኢራን ለዓመታት በአፍሪካ አገራት በሚገኙ የሃይማኖት እና የባህል ተቋማት ላይ ኢንቨስት አድርጋለች። ነጻ የትምህርት ዕድሎችም ሰጥታለች።

  4. ዛሬ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን የተፈጸመው የአየር ጥቃት

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ምዕራባዊ ክፍል ዛሬ ማለዳ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት ተከትሎ በጣም ከባድ ጥቁር ጭስ ሰማዩን ሸፍኖት ነበር።

  5. ኢራን ለተራዘመ ጦርነት መዘጋጀቷን ስትገልጽ፣ ትራምፕ ከጦር መሳሪያ አምራቾች ጋር ሊወያዩ ነው

    ኢራን ጥቃት ከተከፈተባት በኋላ ከአሜሪካ ጋር ለድርድር መቀመጥ እንደማትፈልግ እና ረጅም ጊዜ ለሚቆይ ጦርነት እየተዘጋጀች መሆኗን የሟቹ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ አማካሪ ተናገሩ።

    አማካሪው ሞሐማድ ሞኻባር ዛሬ እንደተናገሩት አገራቸው "ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመደራደር ፍላጎት የላትም፤ ለተራዘመ ጦርነት ተዘጋጅታለች” በማለት ድርድር እንደማይኖር አመልክተዋል።

    ለአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አማካሪው "በአሜሪካኖች ላይ ስለማንተማመን ለድርድር የሚሆን መሠረት የለም። አስከ ፈለግነው ጊዜ ድረስ ጦርነቱን መቀጠል እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአገራቸው ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ዋይት ሐውስ ውስጥ ነገ አርብ ሊነጋገሩ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    በስብሰባው አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ የነበራት ከፍተኛ መጠን ያለው የተተኳሾች ክምችት እየቀነሰ በመምጣቱ ኩባንያዎቹ ምርታቸውን እንዲጨምሩ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ተነግሯል።

    ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎችም ቦታዎች ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመተካት 50 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ በጀት ለመጠየቅ እየተዘጋጀ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካ መንግሥት የጦር መሳሪያ አምራቾች ላይ ምርታቸውን እንዲጨምሩ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚጠበቅባቸውን መጠን እያመረቱ አይደለም የተባሉ ኩባንያዎች ተለይተው እንዲቀርቡ ባለፈው ዓመት አዝዘው ነበር።

    የመከላከያ ሚኒስቴሩ የእነዚህን ኩባንያዎች ዝርዝር ይፋ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ከዚያ በኋላም አስገዳጅ እርምጃ ሊወስድ እና ኮንትራታቸውን ሊያቋርጥ ይችላል።

  6. በሳዑዲው ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ሌላ የድሮን ጥቃት ሙከራ ተደረገ

    ሰኞ ዕለት የኢራን ጥቃት ዒላማ የነበረው ዋነኛው የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የድሮን ጥቃት ሙከራ መደረጉን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።

    የጥቃት ሙከራ ተደርጎበታል የተባለው ‘ራስ ታኑራ’ የነዳጅ ማጣሪያ በሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የነዳጅ ምርት ተቋም እንደሆነ ይታመናል።

    የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስቴር፤ “ጥቃቱ በድሮን እንደተፈጸመ እና ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳላደረሰ የመጀመሪያ ደረጃ ግምቶች አመልክተዋል” ብሏል።

    የነዳጅ ማጣሪያው ከዚህ አስቀሞም በኢራን ጥቃት ተፈጽሞበታል። ሰኞ ዕለት የተነሳ የሳተላይት ምሥል በማጣሪያው ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አሳይቷል። ከጥቃቱ በኋላ የማጣሪያ ተቋሙ ሕንጻ በእሳት ተያይዞ ታይቷል።

    ሰኞ ዕለት የደረሰው የድሮን ጥቃት ተከትሎ ለጥንቃቄ እርምጃ ሲባል “የተወሰነው የነዳጅ ማጣሪው ክፍል” እንዲዘጋ መደረጉን የሳዑዲ መንግሥት አስታውቆ ነበር።

    ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ በሳዑዲ ብቻ ሳይ ሆን በኣለም ዙሪያ ካሉ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከላት አንዱ ነው።

  7. በኢራን ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ መናሩን ቀጥሏል

    ከቀናት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት የታየው የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ የመናር አዝማሚያ አሁንም ቀጥሏል።

    በዛሬው የዓለም አቀፍ ገበያ የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ83.70 ዶላር በላይ ሆኗል። የዛሬው ዋጋ ከትናንቱ ጋር ሲነጻጸር የ2.37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

    ይህ የዋጋ ጭማሪ የተመዘገበው ኢራን የምትቆጣጠረው የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ እና የትራፊክ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ በመጣሉ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለተስተዋለው የነዳጅ ዋጋ ንረት ባደረጉት ንግግር፤ “የነዳጅ ዋጋ ለጥቂት ጊዜ ትንሽ ከፍ ቢልም፤ ይህ [ጦርነት] እንዳበቃ ወዲያውኑ ዋጋው ይቀንሳል” ሲሉ ተደምጠዋል።

    በተጨማሪም “አስፈላጊ ከሆነ” አሜሪካ በመካለኛው መሥራቅ የሚያልፉ መርከቦችን እንደምታጅብ ጠቁመዋል።

    ከዓለም አቀፉ የፔትሮሊየም ላኪ አገራት ድርጅት አባሎች መካከል በርካታ ድፍድፍ ነዳጅ በማምረት ሁለተኛዋ የሆነችው ኢራቅ፤ በቀን ውስጥ የምታመርተውን መጠን በ1.5 ሚሊዮን በርሜል ገደማ መቀነሷን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአገሪቱ የነዳጅ ምርት በግማሽ ገደማ የቀነሰው በነዳጅ ማከማቻ እንዲሁም በኤክስፖርት መስመሮች ላይ በተጣለው ገደብ ምክንያት እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል ተብሏል።

    ኤክስፖርት በድጋሚ የማይጀመር ከሆነ አገሪቱ በየቀኑ የምታመርተውን 3 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ልታቆም እንደምትችልም ተገልጿል።

    በተጨማሪም ኢራን ከዓለም ነዳጅ አንድ አምስተኛው በሚተላለፍበት የሆስሙዝ ሰርጥ ላይ የሚጓዙ የነዳጅ ታንከሮችን የጥቃት ዒላማ አድርጋለች። በሰርጡ በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞም እንደተዘጋ ነው።

  8. የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ትራምፕ ድርድሩን "እንደ ሪል ስቴት ንግድ" ነበር የያዙት አሉ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አግራቺ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በክፋት ተነሳስተው የድርድር ጠረጴዛውን በቦምብ ደብድበዋል” ሲሉ ከሰሱ።

    ​“ውስብስብ የሆኑ የኒውክሌር ድርድሮች እንደ ሪል እስቴት ንግድ ሲያዙ፣ እና ትላልቅ ውሸቶች እውነታን በሚጋርዱበት ጊዜ መሬት የማይወርዱ ነገሮች በፍጹም ሊሳኩ አይችሉም” ብለዋል።

    “ውጤቱስ? በክፋት ተነሳስተው የድርድር ጠረጴዛውን በቦምብ ደብድበዋል” በማለት ጽፈዋል።

    ጦርነቱ ከመጀመሩ ቀናት አስቀድሞ ጄኔቫ ውስጥ ሲደረግ በነበረው ድርድር ቴህራንን ከወከሉ ተደራዳሪዎች ዋነኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አግራቺ ናቸው።

    በዚህ የኒውክሌር ድርድር “ጥሩ መሻሻሎች” እንደተመዘገቡ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ከቀናት በኋላ አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት በመፈጸም ጠቅላይ መሪውን ጨምሮ በርካታ አመራሮችን ገድለዋል።

    ሐሙስ ዕለት ስዊትዘርላንድ ጄኔቭ ላይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር ከተካሄደ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ነበር አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የከፈቱት።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ ጨምረውም "ትራምፕ በዲፕሎማሲ ላይ እና በመረጣቸው የአሜሪካ ሕዝብ ላይ ክህደት ፈጽመዋል" በማለት ጽፈዋል።

  9. ከኻሜኒ ቀብር በኋላ ተተኪያቸው ይታወቃል፣ እስራኤልም አዲሱ መሪን ዒላማ እንደምታደርግ ዝታለች

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ መከናወን የሚጀምር ሲሆን፣ የሚተካቸውም አዲስ መሪ ግብአተ መሪታቸውን ተከትሎ ይፋ እንደሚደረግ የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ምርጫውን የሚያከናውነው ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሲዘገብ፤ እስራኤልም ለደኅንነቷ ስጋት ሆኖ የሚቀጥል መሪ ከተመረጠ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች።

    የጠቅላይ መሪው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሦስት ቀናትን እንደሚወስድ እና ከቀብሩ በኋላ የእስላማዊ ሪፐብሊኩ መሪ የሚሰይሙት መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ያላቸው መሪዎች በአካል ተሰብስበው ምርጫውን እንደሚያከናውኑ ፋርስ የተባለው የዜና ወኪል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ምርጫውን የሚያካሂደው ምክር ቤት አባላት ለአሜሪካ እና እስራኤል እንዳይጋለጡ "አስፈላጊ የሆነው የደኅንነት ጥበቃ እርምጃዎች በከፍተኛ ደረጃ መወሰዱን” ዘገባዎች እየጠቆሙ ነው።

    ነገር ግን 'ቆም' በምትባለው ከተማ የሚገኘው የከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ጉባዔ አባላት ጽህፈት ቤት ማክሰኞ እንዲሁም ቴህራን ውስጥ ስብሰባ የሚያደርጉበት ቦታ ዛሬ በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቃት እንደተፈጸመበት ቢቢሲ ፐርሺያ ዘግቧል።

    የአያቶላህ ኻሜኒ ቀብር በትክክል የት እንደሚካሄድ እስካሁን ያልተገለጸ ሲሆን፣ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ግን ማሻድ በምትባለው ከተማ ውስጥ በሚገኘው ስምንተኛው የሺዓ ኢማም የእምነት ስፍራ ሊሆን እንደሚችል እየዘገቡ ነው።

    የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሦስተኛው ጠቅላይ መሪ ማን እንደሚሆን እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኒው ዮርክ ታይምስ የኢራን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ የሟቹ መሪ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ አዲሱ መሪ እንዲሆን ከስምምነት ላይ መደረሱን እና ይፋ እንደሚደረግ ዘግቧል።

    ፋርስ ዜና ወኪል ከኻሜኒ ቀብር በኋላ የመሪው ማንነት ይፋ እንደሚደረግ እና የሹመት ሥነ ሥርዓቱም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሆን ገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ለአገራቸው ጠላት የሆነ የትኛውም ተተኪ ቢመጣ ዒላማቸው እንደሚሆን ተናግረዋል።

    “እስራኤልን የማጥፋት ዕቅድን የሚቀጥል፣ አሜሪካን ላይ የሚዝት፣ የኢራንን ሕዝብ የሚጨቁን የትኛውም ተተኪ በማያጠራጥር ሁኔታ ለመደምሰስ ዒላማችን ይሆናል” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የአገሪቱን ጠቅላይ መሪ ጨምሮ በርካታ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ያንብቡ ፦ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን የሚተካው ቀጣዩ የኢራን ጠቅላይ መሪ ማን ሊሆን ይችላል?

  10. እስራኤል በቴህራን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት ስትፈጽም፤ ኢራን በኳታር የሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈርን አጠቃች

    የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ለአምስተኛ ቀን በቀጠለበት በዛሬው ዕለት እስራኤል በኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን ስትመታ፣ ኢራን ደግሞ ኳታር ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    እስራኤል ቴህራን ውስጥ የሚገኘውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ አካል የሆነውን የባሲጅ ሚሊሻ ጽህፈት ቤትን እና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማትን ማጥቃቷን የጦሯ ቃል አቀባይ አስታውቋል።

    በተመሳሳይ ኢራን ኳታር ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር ላይ የተነጣጠሩ ሁለት ሚሳዔሎችን መተኮሷን የኳታር የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

    አንደኛው ሚሳዔል በኳታር የአየር መከላከያ ሥርዓት ሲከሽፍ ሌላኛው በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ትልቁ የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር የሆነውን አል ኡዴይዳን መታቱን፣ ነገር ግን በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ታውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዲት የኢራን መርከብ ከሲሪ ላንካ ደሴት አቅራቢያ የመስመጥ አደጋ ደርሶባት የድረሱልኝ ጥሪ ማቅረቧን የሲሪ ካንካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መናጋራቸው ተዘገበ።

    መርከቧ 180 ሰዎችን አሳፍራ በመጓዝ ላይ እንደነበረች እና 30 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ከመርከቧ ወርደው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱም ጨምረው ገልጸዋል።

    ነገር ግን ለኢራኗ መርከብ መስመጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

  11. በመካከለኛው ምሥራቅ ትናንት ምሽት የተፈጸሙ ጥቃቶች

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ለፈጸሙት ጥቃት ቴህራን የአጸፋ ምላሽ መስጠቷን ቀጥላለች። መካከለኛው ምሥራቅን ባዳረሰው ጦርነት ውስጥ ባለፈው ምሽት የተፈጸሙ ጥቃቶች የሚከተሉት ናቸው።

    ኢራን- የኢራን መከላከያ እንዳለው ባለፉት ጥቂት ሰዓታት አዲስ ጥቃቶች መሰንዘር ቀጥሏል። ከኢራን ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ እስራኤል የድንገተኛ ጊዜ ደውል አሰምታለች።

    ሊባኖስ- እስራኤል ሄዝቦላህን ዒላማ አድርጋ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፤ ሄዝቦላህም ትናንት ማምሻውን ሚሳዔሎች ሲተኩስ ነበር። እስራኤል በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች እንደሌሉ ገልጻለች።

    ኩዌት- መኖሪያ ሰፈር አካባቢ በወደቀ የመሣሪያ ስብርባሪ ሳቢያ የ11 ዓመት ልጅ እንደተገደለች የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የታዳጊዋን እናት ጨምሮ አራት ቤተሰቦቿ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች- የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ንግድ ተቋም እንዳለው፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚገኘው ፉጃራህ ወደብ ላይ “ምንነቱ ያልታወቀ መሣሪያ ስብርባሪ” ወድቋል። መርከብ ላይ ጉዳት ቢደርስም የመርከቡ ሠራተኞች እንዳልተጎዱ ተገልጿል።

  12. ኳታር ለኢራን እየሰለሉ ነበር ያለቻቸውን 10 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አዋለች

    የኳታር የፀጥታ ኃይሎች ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ሲሰልሉ የነበሩ “ሁለት የስለላ ሕዋሶችን” ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ሥር ማዋሏን የአገሪቱ የመንግሥት የዜና ወኪል ዘገበ።

    ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሰባቱ “የአገሪቱን ወሳኝ እና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች የተመለከተ መረጃ የመሰብሰብ የስለላ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው” እንደነበረ ዘገባው አመልክቷል።

    በስለላ የተጠረጠሩት ቀሪዎቹ ሦስት ሰዎች ደግሞ “የድሮን አጠቃቀም ሥልጠና የወሰዱ” እንደሆኑ ተገልጿል።

    የዜና ወኪሉ፤ “ተጠርጣሪዎቹ በተደረገባቸው ምርመራ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አምነዋል፤ የስለላ እና የማዳከም ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እንደነበር ተናግረዋል” በማለት ዘግቧል።

    በአሜሪካ እና ኢራን ጥቃት የተከፈተባት ኢራን በሰጠችው የአጸፋ ምላሽ ዒላማ ካደረገቻቸው የቀጣናው አገራት አንዷ ኳታር ነች። ኢራን በፈጸመችው ጥቃት የኳታር ዋነኛ የጋዝ ማምረቻ ተቋም ጉዳት እንደደረሰበት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ሁለት የኢራን ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ ሰባት ሚሳዔሎችን እና አምስት ድሮኖችንም መትቶ እንደጣለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ትናንት በሰጡት መግለጫ “ሁሉም ቀይ መስመሮች ታልፈዋል” ብለው ነበር።

    ጦርነቱ በተጀመረበት ቅዳሜ ዕለት ብቻ ኢራን 65 ሚሳዔሎችን እና 12 ድሮኖችን ወደ ኳታር ማስወንጨፏን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀው ነበር።

  13. እስራኤል “60 የሚገመቱ የሄዝቦላህ ዒላማዎች” ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

    ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠ ያለው ሄዝቦላህ እና እስራኤል አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መረጃ “ ወደ 60 በሚገመቱ የሄዝቦላህ ዒላማዎች” ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ ከገለጻቸው መካከል፤ “የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች፣ የዕዝ ማዕከላት፣ ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች እና ተጨማሪ የሽብር መሠረተ ልማቶች” ይገኙበታል።

    በተጨማሪም ጦሩ፤ በደቡባዊ ሊባኖስ ሁለት አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ የሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ ሌሎች ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ በሰሜን እስራኤል በሚገኘው ሀይፋ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር፤ ሄዝቦላህ ይህንን ካስታወቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባወጣው መረጃ ወደ አገሪቱ የተወነጨፉ በርካታ ተተኳሾች እየመጡ መሆናቸው እንደታወቀ እና አብዛኛዎቹ ተመትተው እንደወደቁ ተናግሯል።

    ከእኩለ ሌሊት በኋላ ደግሞ በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘጋቢ ገልጿል።

    በተጨማሪም እስራኤል በበርካታ የሊባኖስ መንደሮች እና ከተማዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢዎቹን ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች። እስራኤል በዘረዘረቻቸው 13 አካባቢዎች ውስጥ ሄዝቦላህን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንደምትፈጽም ገልጻለች።

  14. ኢራን ውስጥ ከ1,000 በላይ ንጹኃን መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ቡድን ገለጸ

    አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት መፈጸም ከጀመሩበት ቅዳሜ የካቲት 21 አንስቶ ባሉት ቀናት ውስጥ በኢራን ከ1,000 በላይ ንጹኃን መገደላቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል ‘ሂራና’ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ 181 ያህሉ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆነ ሕጻናት ናቸው። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ 5,402 መሆናቸውን የገለጸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ፤ ከእነዚህ ወስጥ 100 ያህሉ ሕጻናት መሆናቸውን አክሏል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ኢራን ውስጥ ቢያንስ 104 ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቡድኑ ገልጿል። እንደ ቡድኑ ዘገባ፤ እነዚህ ጥቃቶች ወታደራዊ ካምፖችን፣ የሕክምና ማዕከላትን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን መትተዋል።

    ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለመሞታቸው የደረሱ መረጃዎች እየተመረመሩ እንደሆነም ተገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ጥቃት በከፈቱበት ቅዳሜ ዕለት በሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት የሞቱ ሰዎችን የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።

    ሚናብ በተባለው የኢራን ከተማ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ትምህርት ቤቱ ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ካምፕ አቅራቢያ እንደሚገኝ ተነግሯል።

    ቢቢሲ በዚህ ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ በገለልተኛነት አላረጋገጠም። የአሜሪካ ጦር ክስተቱን በተመለከተ ስለሚወጡ መረጃዎችን እያጣራ መሆኑን ገልጿል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአካባቢው ላይ ስለተካሄደ ማንኛውም ዘመቻ “እንደማያውቅ” ተናግሯል።

  15. ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኝ የሲአይኤ ጣቢያ በድሮን መመታቱ ተዘገበ

    ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኝ የአሜሪካው የስለላ መሥሪያ ቤት ‘ሴንትራል ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ’ (ሲአይኤ) ጣቢያ በድሮን እንደተመታ ተዘገበ። ጥቃቱን ያደረሱት ድሮኖች የኢራን ናቸው የሚል ጥርጣሬ እንዳለ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በሪያድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሁለት ድሮኖች ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጠዋል። ነገር ግን የስለላ ማዕከሉ የጥቃት ዒላማ ስለመሆኑ የሚያረጋገጥ ምልክት እንደሌለ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካው ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፤ ጥቃቱ የተወሰነውን የኤምባሲውን ጣሪያ “ማፍረሱን” እንዲሁም የሕንጻው ውስጥ በጭስ “መበከሉን” የሚገልጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማግኘቱን አስነብቧል።

    በተጨማሪም ኤምባሲው "መዋቅራዊ ጉዳት" እንደደረሰበት እና ሠራተኞች “ባሉበት መጠለላቸውን እንዲቀጥሉ” እንደተነገራቸው የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል።

    የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከዚህ ጥቃት መዘገብ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ የአገሪቱን ደኅንነት ለመከላከል እና ነዋሪዎቹ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

    የሳዑዲ ካቢኔ አጋር አገራት ከኢራን ሊሰነዘር ለሚችል ለማንኛውም ጥቃት የሚሰጡትን ምላሽ "ለመደገፍ ሁሉንም አቅሞች ለማንቀሳቀስ ያለውን ዝግጁነት" እንዳረጋገጠ የአገሪቱ የዜና ወኪል ዘገባ አመልክቷል።

    የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ከዋና ከተማዋ ሪያድ በስተደቡብ አቅጣጫ ላይ ሁለት ክሩዝ ሚሳዔሎችን ማክሸፉን እንደተናገረ የዜና ወኪሎቹ ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ ዘግበዋል።

    ይፋዊው የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ በበኩሉ ዘጠኝ ድሮኖች እንዲከሽፉ መደረጋቸውን አስታውቋል።

    በተጨማሪም ይፋዊው የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘጠኝ ድሮኖች መመታታቸውን ዘግቧል። የሳዑዲ ባለሥልጣናት እንዲከሽፉ የተደረጉት ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ከየት እንደተተኮሱ አልገለጹም።

  16. አሜሪካ ኢራን ውስጥ ከ1,700 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታወቀች

    ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ በተከፈተው ጥቃት በሦስት ቀናት ውስጥ ከ1,700 በላይ ዒላማዎችን ኢራን ውስጥ መምታቱን የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ያወጣው መረጃ አመለከተ።

    በጥቃቶቹ ዒላማ ከተደረጉት ስፍራች መካከል የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች፣ የባሕር ኃይል መርከቦች፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች እና የመቆጣጠሪያ ማዕከላት ይገኙባቸዋል።

    ማዕከላዊ ዕዙ ጨምሮም ለእነዚህ ጥቃቶች በርካታ ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ የጦር አውሮፕላኖች፣ ሚሳዔሎች እና የጦር መርከቦች ጥቅም ላይ ውለዋል።

    መረጃው በ72 ሰዓታት ውስጥ በኢራን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን፣ በቅድሚያ ዒላማ የተደረጉት “ለዘመቻው እንቅፋት የሚሆኑ ስፍራዎች” እንደሆኑ ተጠቅሷል።

  17. እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት በኢራን ላይ ጥቃት በከፈተችበት ዕለት ድንበር በምትጎራበታት ሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው የኢራን አጋር በሆነው ሄዝቦላህ ላይም ጥቃት ከፍታለች።

    በጥቃቱ የቡድኑን የደኅንነት ኃላፊ እና ሌሎች አባላቱን መግደሏን የገለጸች ሲሆን፣ ሄዝቦላህም በአጸፋው በሰሜናዊ እስራኤል ላይ ሮኬቶችን ተኩሷል።

    በሄዝቦላህ ዳፋ በእስራኤል የሚፈጸመው ጥቃት ያሰጋው የሊባኖስ መንግሥትም ቡድኑ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ማገዱን አስታውቋል።

    ለመሆኑ በመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል የሚባለው እና ለእስራኤል ዋነኛ የራስ ምታት የሆነው እንዲሁም በዋነኛ ባላንጣዋ ኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ማነው?

  18. አባታቸው፣ ሚስታቸው እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው የኻሜኒ ልጅ

    ባለፈው ቅዳሜ የተገደሉት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሥልጣን ተረካቢ ይሆናሉ የተባሉት ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በደኅና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ።

    ሞጅታባ ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው የእስራኤል እና የአሜሪካ ጥቃት አባታቸውን፣ የእንጀራ እናታቸውን፣ ሚስታቸውን፣ እህታቸውን፣ የእህታቸውን ባል እና ሌሎችም የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ተገድለውባቸዋል።

    ሜህር የተባለው የኢራን ዜና ወኪል እንዳለው ሞጅታባ ኻሜኒ “በአሁኑ ጊዜ የተሰዉ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጉዳይ በመከታተል፣ በማማከር እና የአገሪቱን ጠቃሚ ጉዳዮችን በማከናወን ላይ ናቸው።”

    ከአራት ቀናት በፊት የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ ቤት እና ጽሕፈት ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት አባታቸው ሲገደሉ፤ የእንጀራ እናታቸው ማንሱሬህ ኾጃስትህ ባግህርዛዴህ ደግሞ በጥቃቱ ክፉኛ ተጎድተው ኮማ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

    እንዲሁም ሚስታቸው ዛሃራ ሃዳድ አዴል፣ ሴት ልጃቸው፣ የልጃቸው ባል እና የልጃቸው ልጅ በጥቃቱ ተገድለውባቸዋል።

    የ53 ዓመቱ ሞጅታባ የሟቹ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሁለተኛ ልጅ ሲሆኑ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢራንን የመሪነት ሥልጣን ይይዛሉ ተብለው በተደጋጋሚ ሲነሱ ቆይተዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከመክፈታቸው ከሳምንት በፊት በወጡ ዘገባዎች ላይ አሜሪካ ጦርነት የምትጀምር ከሆነ ቀዳሚ ዒላማ የምታደርገው የአገሪቱን መሪዎች እንደሚሆን፣ ዋነኞቹ ደግሞ አያቶላህ ኾሜኒ እና ልጃቸው ሞጅታባ ኾሜኒ እንደሆኑ ተጠቅሶ ነበር።

  19. ጦርነቱ እስከ መቼ ሊቀጥል ይችላል?

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እየተስፋፋ ነው።

    ኢራን በበኩሏ በቀጣናው ወደሚገኙ አገራት ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ተጠቅማ ጥቃት መፈጸም ጀምራለች።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የዓለማችን ዋነኛ የነዳጅ ማውጫ፣ ማጣሪያ እና ማስተለላፊያ ተቋማት እንዲሁም የባሕር መስመሮች የኢራን ጥቃት ዒላማ በመሆናቸው መስተጓጎል ገጥሟል።

    አሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ ጦርነቱ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል? የሚለው ሆኗል።

    አሜሪካ እና አስራኤል ያቀዱትን እስከሚያሳኩ እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ የተፈጸመባትን ጥቃት በመቀልበስ ጠላቶቿን ዋጋ እንደምታስከፍል እየዛተች እና የአጸፋ እርምጃም እየወሰደችው ነው።

    ለመሆኑ ጦርነቱ እስከመቼ ሊቆይ ይችል? የሚለውን ለመረዳት ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ፦ ጦርነቱ ለምን ያህል ጊዜ ሊካሄድ ይችላል?

  20. የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የምግብ ዋጋን እንደሚያንር ተገለጸ

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ ከመጨመሩ ባሻገር የምግብ ዋጋም ሊንር እንደሚችል ተጠቆመ።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ መቀጠሏ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድሯል።

    ይህም በሰብል እህሎች ምርት እንዲሁም ዝውውር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

    የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት የበቆሎ፣ የስንዴ እና የሩዝ ዋጋ እንዲንር ያደርጋል። በሌላ በኩል ማዳበሪያ ለመሥራት የሚውለው ኬሚካል (ዩሪያ) እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ገልጸዋል።

    ከዩሪያ ምርት አንድ ሦስተኛው የሚዘዋወረው በባሕር ላይ ነው።

    ከማዳበሪያ አምራች ድርጅቶች ሁለተኛ ትልቁ የሆነው ‘ያራ’ ኃላፊ የሆኑት ስቬን ቶሬ ሆልስተር “አንዳንድ የሰብል ዓይነቶች ምርታቸው 50% ሊቀንስ ይችላል” ብለዋል።

    የሆርሙዝ ሰርጥ የተዘጋበት ጊዜ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ችግሩን እንደሚያባብሰውም አክለዋል።