ኤንፋሊ ኮይቴ፡ ለሙዚቃ መሳሪያው መሰበር የእንግሊዝ አየር መንገድን ተጠያቂ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Michael Palmer
ሙዚቀኛ ኤንፋሊ ኮይቴ "በትእዛዝ፣ በልዩ ሁኔታ ነው ተሰራ" የሚለውን የሙዚቃ መሳሪያ በአውሮፕላን እቃ መጫኛ ውስጥ ተገዶ ከጫነ በኋላ ክፉኛ ለመሰባበሩ የእንግሊዝ አየር መንገድን ተጠያቂ አደረገ።
በምእራብ አፍሪካ ታዋቂነት ያለው 'ኮራ' (የአፍሪካ በገና) የተባለውን የሙዚቃ መሳሪያው በኤሌክትሪክ እንዲሰራ ተደርጎም ዲዛይን ተደርጎለታል።
ሙዚቀኛው እንደሚለው በእጅ ይዞ ለመንቀሳቀስ በሚያመች መልኩ ከመሰራቱ አንፃር በበረራ ወቅትም በአውሮፕላኑ ውስጥ ባለው የእቃ ማስቀመጫ ኪስ እንዲቀመጥ ተደርጎ የተሰራ ነው።
ይሁን እንጂ በአውሮፕላኑ ከባድ እቃዎች መጫኛ ውስጥ እንዲጭን በመገደዱ የሙዚቃ መሳሪያው ከጥቅም ውጭ እንደሆነበት ይናገራል።
በመሳሪያው ዳግም ሊጫወትበት እንደማይችል የሚያስረዳው ሙዚቀኛው በሌላ ለመተካት አሊያም ለመጠገን የእንግሊዝ አየር መንገድ ሊከፍለኝ ይገባል ብሏል።
የእንግሊዝ አየር መንገድ በበኩሉ ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነ ገልጿል።
ጊኒያዊው ሙዚቀኛ ኮይቴ ይህ ያጋጠመው በእንግሊዝ የሙዚቃ ሥራውን ካቀረበ በኋላ በጎርጎሳውያኑ ነሐሴ 18 ከእንግሊዝ አየር መንገድ ሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ብራስልስ እየተጓዘ ሳለ ነበር።
የሙዚቃ መሳሪያው 80 ሴንቲ ሜትር በ20 ሴንት ሜትር ርዝመት ያለውና 6 ኪሎግራም የሚመዝን ሲሆን በአውሮፕላን ማረፊያው የነበሩ ተቆጣጣሪዎች በእጅ ተይዞ የሚገባ እቃ እንደሆነ እንደነገሩት ይገልፃል።
ይሁን እንጂ ወደ በረራ የሚገባበት መግቢያ ከደረሰ በኋላ አንድ የአየር መንገዱ ሠራተኛ መሣሪያው በአውሮፕላኑ እቃ መጫኛ መግባት እንዳለበት መንገሯንም ገልጿል።
22 ክሮች ያሉትና ተሰባሪ የሙዚቃ መሳሪያ እንዴት በእቃ መጫኛ ውስጥ ሊገባ ይችላል የእርሱ ሙግት ነበር፤ ይሁንታን ግን አላገኘም።

የፎቶው ባለመብት, N'Faly Kouyate
"ከሁለት ቀናት አስቀድሞ ከብራስልስ ወደ ለንደን ሳመራ በእጀ ይዤው እንደገባሁ ለአየር መንገዱ ሰራተኛ ነግሬያታለሁ" ይላል-ኮይቴ።
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት እንደገዛው የሚናገረውን የሙዚቃ መሳሪያ በትኛውም አየር መንገድ በእጁ ይዞት ሲገባ የተቃወመው እንዳልነበርና ይህ ለመጀመሪያ ጊዜው እንደሆነ ቢነግራትም ሰራተኛዋ "ሕጉ ተለውጧል" ስትል ምላሽ እንደሰጠችው ያክላል።
መሳሪያው አውሮፕላኑ እቃ መጫኛ ውስጥ እንዳይገባ የሚፈልግ ከሆነ አውሮፕላኑን እንደማይሳፈር እንዳስጠነቀቀችው ለቢቢሲ ተናግሯል።
የወላጆቹ የመቃብር ስፍራ ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዛወሩ ምክንያት ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ ትውልድ ሃገሩ ጊኒ ለማምራት እቅድ ስለነበረውም ሊቃወማት አልቻለም።
ኬይቴ የኮራ ሙዚቃ መሳሪያ ንጉስ ሲሉ በርካቶች ያሞካሹታል።
የሙዚቀኛው የሥራ ባልደረባ ሳይመን ኤመርሰን እንደሚለው የሙዚቃ መሳሪያው የተሰራበትን የፈረንሳይ ድርጅት ምላሽ እየተጠባበቁ ሲሆን መሳሪያው እንደማይጠገን አስረግጠው ነግረዋቸዋል። 4500 ፓውንድ እንደሚያወጣ አክሏል።
የሙዚቀኞች ማህበሩ በበኩሉ " በተለያየ ጊዜ ሙዚቀኞች የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው ወደ አውሮፕላን ሲገቡ ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥማቸው እንሰማለን፤ የአየር መንገዱ ሰራተኞችም ከሕጉ ውጭ የራሳቸውን ፍላጎት ተግባራዊ ሲያደርጉ ይታያል" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
"ሠራተኞቻችን ለመንገዶኞቻችን እቃዎች ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ ይህንን በመስማታችን በጣም ነው ያዘነው ፤ ጉዳዩን በአስቸኳይ እናጣራለን ፤ የደንበኞች አገልግሎት ቡድንም ሙዚቀኛውን አግኝቶ በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት ይሞክራሉ" ሲል የእንግሊዝ አየር መንገድ ምላሽ ሰጥቷል።












