አዲሱ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ የሕግ ማስከበር አገልግሎትን እንዴት ይቀይራል?

በፖሊስ ጣቢያው ግርግር አይስተዋልም። በጭንቀት የተዋጡ ሰዎች የሉም። ፖሊሶች የስም ዝርዝር ይዘው አይጠሩም።
የተለመደው የፖሊስ ጣቢያ ድባብ በሌለው አዲስ ፖሊስ ጣቢያ የሚታዩት በተለያየ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የኮምፒውተር ወይም ታብሌት ስክሪኖች ናቸው።
በአዲስ አበባ በሙከራ ላይ ካሉ ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያዎች ቦሌ የሚገኘው አንዱ ነው። እነዚህ 'ስማርት' ፖሊስ ጣቢያዎች የአገሪቱ 'የዲጂታል አብዮት' አካል ናቸው ተብሏል።
በፖሊስ ጣቢያው መግቢያ ላይ በተሰቀለ ስክሪን የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክት ይነበባል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምሥልም ይታያል።
በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙ የፀጥታ ባልደረቦች ዲጂታል ሥርዓቱ እንዴት እንደሚሠራ ያስጎበኛሉ። ፖሊስ ጣቢያው የቴክኖሎጂ ማዕከል የሚመስል ገጽታ አለው።
የፖሊስ ጣቢያው የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ እንደሚሉት፤ በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙ የፀጥታ ባልደረቦች ሰዎች "እንዲለማመዱ" እገዛ ይሰጣሉ።
ኮማንደር ደምሴ አንድ ክፍል ውስጥ ገብተው ስክሪን በመንካት ሪፖርት ያደርጋሉ። ክስተቱ ወንጀል፣ የትራፊክ አደጋ ወይም ሌላ ስጋት መሆኑን ለማወቅ በስክሪኑ ላይ ከሚቀርቡላቸው ዝርዝሮች መካከል ይመርጣሉ።
ከዝርዝሩ አንዱን ከመረጡ በኋላ አስተያየት እንዲሰጥበት ሪፖርቱን ያስገባሉ።
ሌላ ቦታ የሚገኝ የፖሊስ ባልደረባ በስክሪኑ ላይ መጥቶ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ጥያቄዎች ያቀርባል። ጥያቄዎቹን የሚጠይቀው ቻትቦት ሳይሆን የፀጥታ ባልደረባ የሆነ ሰው ነው።

"ችግር ካለ የፀጥታ ባልደረቦች በአፋጣኝ ሪፖርት ወደተደረገው ቦታ ይደርሳሉ" ሲሉ ኮማንደር ደምሴ ያስረዳሉ።
ስማርት ፖሊስ ጣቢያው ሥራ በጀመረበት የመጀመሪያ ሳምንት ሦስት ሪፖርቶች ተቀብሏል። እነዚህም የጠፋ ፓስፖርት፣ የፋይናንስ ማጭበርበር እና ቅሬታ ናቸው።
ስለ ፖሊስ ጣቢያው ያለው ግንዛቤ ሲጨምር ብዙ ጥቆማዎች እንደሚያስተናግድ ኮማንደር ደምሴ ያምናሉ።
"በቀጣይ የፖሊስ አገልግሎት ለሕዝቡ በቅርበት ተደራሽ መሆን አለበት" ይላሉ።
ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ወንጀሎች ሪፖርት ሲደረጉ ያለውን የሰው ለሰው ግንኙነት ይቀንሳል። ሆኖም ግን በቂ የፀጥታ ባልደረቦች በሌሉባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች የሕዝብ ተደራሽነት እንደሚያሰፋ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስማርት ፖሊስ ጣቢያዎችን ባስተዋወቁበት ንግግር፤ ሕግ የማስከበር ሒደትን እንደሚያሻሽል ጠቁመዋል።
የመጀመሪያውን ስማርት ፖሊስ ጣቢያ አገልግሎት የጀመረው የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ. ም. ሲሆን፤ የፖሊስ አገልግሎት "በተሻለ ፍጥነት እና በቴክኖሎጂ ታግዞ" ለዜጎች እንደሚደርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' በሚል የአምስት ዓመት ዲጂታል ስትራቴጂ ካስተዋወቀች በኋላ የመታወቂያ፣ የክፍያ ሥርዓት፣ የፍርድ ቤት እና ሌሎችም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ዲጂታል የማድረግ ንቅናቄ ጀምራለች።
የኢንተርኔት ተደራሽነት ውስን የሆነባት ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንጻር በቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደኋላ ቀርታለች። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተቀሰቀሱ ግጭቶች እና ጦርነት ምክንያት ኢንተርኔት በተደጋጋሚ ተቋርጧል።
በሌላ በኩል የቴሌኮም ዘርፉ እየተሻሻለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተስፋፍቷል። አገር አቀፍ መታወቂያ ዲጂታል መሆኑ እና የመንግሥት ተቋማት የበይነ መረብ አገልግሎትም ተጠቃሽ ለውጦች ናቸው።
ይሄንን ዲጂታል አሠራር የሚደግፉ ሰዎች፤ የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ በሆነባት አገር እየታየ ያለው ለውጥ እንዲያውም ዘግይቷል ብለው ይከራከራሉ።
ሶፍትዌር ኢንጂነር የሆነው ብርሃን ነጋ እየታየ ባለው ለውጥ ደስተኛ ነው። "ሥራው በአግባቡ ሲከናወን ቢሮ መሄድን እና የወረቀት ምልልስን ያስቀራል" ይላል።
ሆኖም ከደኅንነት አንጻር ስጋቶችም አሉት። "ዲጂታል ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች በቀላሉ ሊጭበረበሩ ይችላሉ" ሲልም ያስረዳል።
በብዛት ተጠቃሚ የሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ የንግድ ተቋማት እና በአጠቃላይ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ይናገራል።
ሆኖም ግን "አዛውንቶችን፣ የገጠር ነዋሪዎችን እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን ያካተተ አይደለም" ይላል።
በኢትዮጵያ ያለው ዲጂታል ተደራሽነት የተመጣጠነ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 79% የኢንተርኔት አገልግሎት አያገኝም።
የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ተንታኝ የሆነው ዘላለም ግዛቸው እንደሚለው፤ መንግሥት የዘረጋው ስትራቴጂ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ልዩነትን እያጠበበ ነው።
"የዲጂታል ዕውቀት ውስንነት አሁንም ፈተና ነው። ስለዚህም የ'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' ስትራቴጂ ትኩረት በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ሳይሆን ሥልጠና መስጠትንም ይጨምራል" ሲል ያብራራል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ዘላለም ይናገራል።
"ዲጂታል ክፍያ በትሪሊዮን ብር አድጓል። የኢንተርኔት ተደራሽነት በጣም ጨምሯል። ከ130 በላይ የመንግሥት ተቋማት ዲጂታል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በዘርፉ ትልቅ ኢንቨስትመንት አለ። ያለ መሠረተ ልማት፣ ፖሊሲ እና ክህሎት የሕዝብ አገልግሎት ዘርፍ አይዘምንም" ይላል።
አሁን ላይ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ በሙከራ ደረጃ ነው የሚገኘው።
ገና በመዘርጋት ላይ ያለውን ዲጂታል አሠራር ለዜጎች እያስተዋወቁ ያሉት የፀጥታ ባልደረቦች ናቸው። አብዛኛው ማኅበረሰብ አሁንም ፖሊስ ጣቢያ በአካል በመሄድ ጥቆማ ይሰጣል።
ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ምን ያህል ይስፋፋል? የሚለውን ለማወቅ በፖሊስ ጣቢያው ማንም የፀጥታ ባልደረባ ሳይኖር የሚገለገሉ ሰዎችን ቁጥር መመልከት ያስፈልጋል።
ቦሌ የሚገኘው ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ገና ሙከራ ደረጃ ላይ ነው። ምናልባትም የኢትዮጵያ ዲጂታል ሕልም ምን እንደሚመስል ለመመልከት መጠነኛ መስኮት ልንለው እንችላለን።












