ዊልቼር የሚጠቀመው ኬንያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጉላልቶኛል አለ

ሃሩን ሃሰን

የፎቶው ባለመብት, Harun Hassan

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የዊልቼር ተጠቃሚ የሆነው ኬንያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጉላልቶኛል አለ።

ከናይሮቢ ወደ አሜሪካ ሊጓዝ የነበረው ኬንያዊ ጸሃፊ ሃሩን ሃሰን፤ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ክልከላ እንደተፈጸመበትና ድጋፍ እንዳልተደረገለት ተናግሯል።

ደራሲና የአካል ጉዳተኞች መብት ተቆርቋሪ የሆነው ሃሩን "መስተናገድ በማይገባኝ መልኩ ተስተናግጃለሁ" በማለት በትዊተር እና በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል። አንድ የአየር መንገዱ ሠራተኛ "ረዳት ለሌለው አካል ጉዳተኛ ጉዞ አንፈቅድም" እንዳለችውም ገልጿል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ሃሩን እንደሚለው፤ በአውሮፕላን ትኬቱ ላይ አካል ጉዳተኛ መሆኑ እና በእራሱ በዊልቼር በመታገዝ እንሚንቀሳቀስ በግልጽ እንደሚታይ ተናግሯል። ይህ ሆኖ ሳለ ግን አየር መንገዱ ውስጥ የገጠመው ከዚህ የተለየ እንደሆነ ያስረዳል።

"ያለምንም ረዳት ብቻየን ተውኝ" የሚለው ሃሩን፤ "ይህ ድርጊት የኬንያ አየር ማረፊያ ፖሊሲን፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብሯቸው የሚሠራቸው ሌሎች ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኛ ተጓዦችን ሕጎችንም የሚጻረር ነው" በማለት ጉዳዩ ከሕግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል።

ይህንን ወቀሳ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከጻፈ ከ10 ሰዓታት በኋላ አየር መንገዱ የቢዝነስ ክፍል በመስጠት እንደሚክሰው እና በማኅበራዊ ሚዲያ የጻፈውን ወቀሳ እንዲያጠፋ መጠየቃቸውን ሃሩን ተናግሯል። "በምቾት መጓዙ ቀርቶብኝ ከነክብሬ በኢኮኖሚ ክፍል ውስጥ ሆኜ ብጓዝ ይሻለኛል" የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ ብሏል።

ሃሩን እንደሚለው፤ ኢ-ፍትሃዊነትን በተመለከተ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ለሕዝብ ሲያደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው። "በየቀኑ ከዚህም የሚበልጡ በደሎችና መገለሎች ይገጥሙኛል። ይህኛው ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች የሚደርስባቸውን ያልተገባ መስተንግዶን ያሳያል" ብሏል።

ቅሬታውን በማኅበራዊ ሚዲያ የጻፈው "ሁሉን ማቀፍ የምትችል ዓለም ለመፍጠር" እንደሆነም ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጂ አየር መንገዱ ሃሩን ሃሰን ካሰፈረው የትዊተር ጽሁፍ ሥር ለደረሰበት መጉላላት ይቅርታ በመጠየቅ፤ ጉዳዩን ለመመርመር የአየር ጉዞ ዝርዝሩን እና አድራሻውን እንዲልክ ጠይቋል።