የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የኢራንን መንግሥት በመቃወም ራሱን አጠፋ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ታዋቂው ኢራናዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኪያኖሽ ሳንጃሪ የኢራንን መንግሥት በመቃወም ራሱን አጠፋ።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምባገነን ነው ያለውን የኢራኑን የአያቶላ አሊ ኻሚኒ አስተዳደር በመቃወም ራሱን አጥፍቷል።

አራት የፖለቲካ እስረኞች እስከ እሮብ ምሽት ከእስር ካልተለቀቁ ራሱን እንደሚያጠፋ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስታውቆ ነበር።

ሕይወቱ ማለፉን አጋሮቹ የሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አስታውቀዋል።

“አንድ ቀን ኢራናውያን ነቅተው ባርነትን ያሸንፋሉ” ሲል ራሱን ከማጥፋቱ አስቀድሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፏል።

የኢራንን መንግሥት አጥብቶ በመተቸት የሚታወቀው ኪያኖሽ ሳንጃሪ ለዴሞክራሲ ሲታገል ቆይቷል።

ከመሞቱ በፊት “ማንም ሰው ሐሳቡን በመግለጹ ምክንያት መታሰር የለበትም። መቃወም የሁሉም ኢራናውያን መብት ነው” ብሏል።

ፋትሚ ሰፕሀሪ፣ ናስሪን ሻክራሚ፣ ቶማጂ ሳሊህ እና አርሻም ረዛይ ከእስር ቤት የማይለቀቁ ከሆነ “የኻሚኒን መንግሥትና አጋሮቹን በመቃወም ራሴን አጠፋለሁ” ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ጽፎ ነበር።

አራቱም የታሰሩት የ22 ዓመቷ ማሳ አሚኒ መገደሏን ተከትሎ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በመደገፋቸውና በመሳተፋቸው ነበር።

እአአ በ2022 ማሳ አሚኒ በኢራን የሞራል ፖሊስ ከታሰረች በኋላ መሞቷን ተከትሎ በኢራን ሕዝባዊ ቁጣ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል።

ኪያኖሽ ሳንጃሪ በፖለቲካ ንቅናቄው ምክንያት ከ1999 እስከ 2007 ታስሮ ነበር።

በ2007 በኖርዌይ የጥገኝነት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቷል። ከዚያም በዋሽንግተን ዲሲ ለቪኦኤ ፐርዥያን ሠርቷል።

በ2016 ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ኢራን ተመልሷል። ታስሮ በኢቪን እስር ቤት 11 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ይህ እስር ቤት የፖለቲካ እስረኞች የሚታሰሩበት ነው።

በ2019 ከጤናው ጋር በተያያዘ በዋስ ተለቋል። ወደ አእምሮ ሕክምና እንዲወሰድም ተደርጓል።

ኪያኖሽ ለኢራን የአገር ውስጥ መገናኛ እንደገለጸው የኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲሁም ከአልጋ ጋር እስራት ተፈጽሞባል። በርካታ መድኃኒቶችም ተሰጥተውታል።

የንግግር ነጻነት ተሟጋቹ ሁሴን ሮናጊ በኤክስ ገጹ ላይ “ኪያኖሽ ሳንጃ ስም ብቻ አይደለም። የዓመታት ስቃይ፣ አይበገሬነትና የነጻነት ትግል ምልክት ነው” ሲል ጽፏል።