ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩኬ የቤት አልባነት ሚኒስትሯ የግል ቤታቸው ላይ ኪራይ ጨምረዋል በሚል ከስራ ለቀቁ
በዩናይትድ ኪንግደም የቤት አልባነት ሚኒስትር ሩሻናራ አሊ የግል መኖሪያ ቤታቸው ላይ ኪራይ ጨምረዋል በሚል ትችት መቅረቡን ተከትሎ ከስራ መልቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ አረጋገጠ።
ሚኒስትሯ በምስራቅ ለንደን የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ የአከራዮችን ውል አቋርጠው የኪራይ ጭማሪ በማድረጋቸው "የግብዝነት አካሄድ ተከትለዋል በሚል ወቀሳ መቅረቡን ተከትሎ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው።
ሩሻናራ አሊ ከቤት አልባነት በጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጭምር ግፊት ጫና መጥቷል።
ሚኒስትሯ ለዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ "ሁልጊዜም ቢሆን አስፈላጊ የሆኑ ህጋዊ መስፈርቶችን እከተላለሁ" ሆኖም በዚህ ኃላፊነት ላይ መቆየት "መንግሥት ከሚሰራው ታላቅ ስራ እንቅፋት መሆን ነው" ብለዋል።
የዚህ ውዝግብ መነሻ የሆነው ሚኒስትሯ መኖሪያ ቤታቸውን ለመሸጥ ሲሉ የተከራዮቻቸውን ቋሚ ውል ቢያቋርጡም ነገር ግን በስድስት ወራት ውስጥ ቤታቸውን በከፍተኛ ዋጋ ለማከራየት በድጋሚ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሯ የፈጸሙት ተግባር በተከራዮች መብት ህግ መሰረት ህገወጥ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉት ጉዳይ ነው።
ይህንን ዘገባ መጀመሪያ ያወጣው አይ ፔፐር የሚኒስትሯን ቤት ተከራይታ የነበረች ግለሰብ በህዳር ወር ላይ ቀጣዩ የኪራይ ሊዝ እንደማይታደስና አራት ወራትም እንዳሏት ኢሜይል እንደደረሳት ተዘግቧል።
እሷ እና ሶስት ተከራዮች የሚኒስትሯን መኖሪያ ቤት ከለቀቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቤቱ ከነበረው በ700 ፓውንድ ጭማሪ እንዲከራይ ተመዝግቧል።
ሚኒስትሯ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ "ከሚኒስትርነት ለመልቀቅ ያቀረብኩት ጥያቄ በከባድ ኃዘን ነው" ብለዋል።
ሁልጊዜም ህጋዊ ሁኔታዎችን ይከተሉ እንደነበር አጽንኦት ሰጥተው "ኃላፊነቴን እና ግዴታዎቼን ተከትዬ እንደሰራሁ አምናለሁ፤ እውነታውም ይህንን ያሳያል" በማለት ደብዳቤው ላይ አስፍረዋል።
"ሆኖም በእዚህ ኃላፊነት መቀጠል የመንግሥትን ትልቅ ስራ እንደሚያደናቅፍ ግልጽ ስለሆነ ከሚኒስትርነቴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ" ብለዋል።
ለስልጣን መልቀቂያዋ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር "ትጉህ" ሰራተኛ በማለት ላከናወኗቸው ተግባራት አመስግነዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎዳና ላይ ማደርና መለመንን ወንጀል ያደረገውን ቫግራናንሲ አክትን ለመሻር ላደረጉት ተግባር ምስጋናቸውን ገልጸው "መንግሥትን ከጀርባ ሆነሽ መደገፍሽን እንደምትቀጥይና የመራጮችሽን ጥቅም በመወከል እንደምትሰሪ አውቃለሁ" ብለዋል።
ለሚኒስትሯ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በበኩላቸው መኖሪያ ቤታቸው ለሽያጭ መቅረቡን ተከትሎ ተከራዮች ቋሚ ውል ሳይሰጣቸው እንዲቆዩ ቢጠየቁም ፍላጎት አለማሳየታቸውን ተናግረዋል።
መኖሪያ ቤቱ ለሽያጭ ዘንድሮ ህዳር ወር ላይ በ915 ሺህ ፓውንድ የቀረበ ሲሆን ያም ዋጋ በየካቲት ወር ላይ 20 ሺህ ፓውንድ ቢሆንም መሸጥ ስላልቻለ እንደገና ለኪራይ መውጣቱን አይ ፔፐር ዘግቧል።
መንግሥት በረቂቅነት ያቀረበው የተከራይ መብት ህግ በፓርላማ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አከራዮች ቤታቸውን ለመሸጥ ሲሉ ውላቸውን ካቋረጡ ከስድስት ወራት በኋላ እንደገና ማከራየትን የሚከለክል ነው።