ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻትጂፒቲን የፈጠረውን ተቋም ያጋለጠው የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ ሞቶ ተገኘ
ኦፕንኤአይን ያጋለጠው የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኝ መኖሪያ ውስጥ ሞቶ መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
የ26 ዓመቱ ሱቺር ባላጂ አስክሬን የተገኘው ፖሊስ ደኅንነቱን እንዲያጣራ የስልክ ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነበር።
የሳን ፍራንሲስኮ ሐኪም ሱቺር ራሱን እንዳጠፋ ገልጿል። ፖሊስም ይህንን የሚጻረር ማስረጃ አለማግኘቱን ገልጿል።
ሱቺር ባለፉት ጥቂት ወራት የኦፕንኤአይን አሠራር ሲቃወም ነበር።
ኦፕንኤአይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋም ሲሆን በዋናነትም ቻትጂፒቲን በመፍጠሩ ይታወቃል።
ኦፕንኤአይ የግል መረጃ የሚሰበስብበትን መንገድ በተመለከተ ብዙ ክሶች በፍርድ ቤት ቀርበውበታል።
ኒው ዮርክ ታይምስ ባለፈው ጥቅምት ባተመው ቃለ ምልልስ ላይ የቀድሞ የኦፕንኤአይ ሠራተኛው ሱቺር ድርጅቱ ቻትጂፒቲን ሲሠራ የአሜሪካን የቅጂ መብት መጣሱን ተናግሯል።
ሱቺር ለአራት ዓመት በድርጅቱ ውስጥ በተመራማሪነት ሠርቷል።
"የቅጂ መብትን በመጣስ ነው ቻትጂፒቲ የተሠራው። ሕግ የጣሰ ነው። እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በይነ መረብ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ" ሲልም ተናግሯል።
ኦፕንኤአይ በበኩሉ የሚሠራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች "ለሕዝብ ይፋ የሆነ መረጃ" ላይ የተመረኮዙ ናቸው ብሏል።
ሱቺር ኦፕንኤአይን የለ ቀቀው ያለፈው ነሐሴ መሆኑን ለኒው ዮርክ ታይምስ ገልጿል። የራሱን ፕሮጀክቶች እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል።
በካሊፎርንያ ያደገው ሱቺር በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርንያ፣ በርክሊ ተምሯል።
የኦፕንኤአይ ቃል አቀባይ "ይህንን ዜና በመስማታችን ልባችን ተሰብሯል። ለሱቺር ወዳጆች በዚህ ከባድ ጊዜ መጽናናትን እንመኛለን" ማለታቸውን ሲኤንቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካ እና ካናዳ አሳታሚዎች ኦፕንኤአይ መተግበሪያዎቹን ለማሠልጠን በሕገ ወጥ መንገድ ዘገባዎቻችንን ወስዷል ሲሉ ከሰዋል።
በዚህ ክስ ውስጥ ኒው ዮርክ ታይምስና የዝነኛው ደራሲ ጆን ግሪሻም አሳታሚዎች ይገኙበታል።
ኦፕንኤአይ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ "ዓለም አቀፍ የቅጂ መብትብ በማክበርና ለፈጠራ ባለቤቶች ፍትሐዊ መሆነ መንገድ ነው የምንሠራው" ብሏል።