የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ትራምፕ ከኃላፊነታቸው ሊያባርሯቸው በመሞከራቸው ክስ መሰረቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፌደራል ሪዘርቭ ተብሎ ከሚጠራው የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ሰባት ገዢዎች መካከል አንዷ የሆኑት ሊሳ ኩክ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሥልጣን ሊያባርሯቸው ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ ክስ መሰረቱ።
ይህ የሕግ ክርክር የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ምን ያህል ነጻ ነው የሚለውን ያሳያል ተብሏል።
ኩክ ፍርድ ቤቱ የዶናልድ ትራምፕን ከሥልጣን የማባረር ትዕዛዝ "ሕገ ወጥ እና ተቀባይነት የሌለው" በሚል እንዲሽረው የጠየቁ ሲሆን በምስክርነት የማዕከላዊ ባንክ ሊቀመንበሩን ጄሮሜ ፖውልን ጠርተዋል።
ትራምፕ በቤት ግዢ የብድር ስምምነቶች ላይ የተሳሳተ መግለጫ ለማውጣታቸው አሳማኝ የሆነ "በቂ ምክንያት" አለ ካሉ በኋላ፤ ገዥዋን ከኃላፊነታቸው ለማንሳት ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም እርሳቸውን ከሥልጣን ለማስነሳት የሚያስችል "በሕጉ ላይ የተቀመጠ አንዳችም ምክንያት የለም" ብለው ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፌደራል ሪዘርቭ ላይ ጫናቸውን እያጠናከሩ ሲሆን፤ በተለይም የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኛ ባልሆኑት ሊቀ መንበሩ ጅሮም ፓውል ላይ ባለፉት ሳምንታት ጫናቸውን እያሳደሩ ነው።
ኩክ በአሜሪካ የወለድ ምጣኔን የመተመን ኃላፊነት ያለበት ቦርድ አባል ናቸው።
የሐሙሱ ክስ ወደ አሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚያመራ በርካታ የሕግ ተግዳሮቶችን ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
"ይህ ክስ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ታይቶ የማያውቅ እና ሕገወጥ ገዥዋን ኩክን ከሥልጣንዋ ለማንሳት የተደረገ ሙከራ ለመቃወም የቀረበ ነው፤ ይህ እንዲሆን ከተፈቀደ በቦርዱ ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያው ይሆናል" ሲሉ የኩክ ጠበቃ አቤ ሎውል በክስ ማመልከቻቸው ላይ ጽፈዋል።
"የፌዴራል ግምጃ ቤት ሕግን ይለውጣል. . . ሕጉ አንድ ገዥ ከሥልጣን እንዲወርድ ለማድረግ 'ምክንያት' ማቅረብን በግልፅ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም ገዥዋ ኩክ የሴኔት ይሁንታን ከማግኘታቸው በፊት በቤት ግዢ የብድር ስምምነቶች ላይ የተሳሳተ መግለጫ ለማውጣታቸው የቀረበው ማስረጃ ይህንን የሚያሟላ አይደለም" ሲሉ ሎውል በማመልከቻቸው ላይ አብራርተዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኩሽ ዴሳይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ኩክን "ከሥልጣናቸው ለማባረር በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን ነው የተጠቀሙት" ብለዋል።
"ፕሬዚዳንቱ በተጨባጭ የፋይናንስ ተቋማትን በሚቆጣጠረው ተቋም ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ያላቸው ግለሰብ በፋይናንስ ሰነዶች ላይ በመዋሸታቸው ገዢዋን ለማባረር በቂ ምክንያት መኖሩን ወስነዋል" ብለዋል።
"በምክንያት አንድ ገዥ ከሥልጣን ማንሳት የፌደራል ሪዘርቭ ቦርድ ለአሜሪካ ሕዝብ እና ለገበያው ያለውን ተጠያቂነት እና ታማኝነት ያሻሽላል።"
የፌደራል ግምጃ ቤት ሕግ የብሔራዊ ባንክ ገዢዎችን በዘፈቀደ እንዲያባርሩ አይፈቅድም፤ ትራምፕ ግን "ምክንያት እስካለ ድረስ" ለማባረር ሥልጣን አንደሚሰጣቸው ይናገራሉ።
በኩክ ላይ የቀረበው ውንጀላ መጀመርያ ለሕዝብ ይፋ በሆነ ደብዳቤ የተገለፀው የትራምፕ ደጋፊ በሆኑት ቢል ፑልቴ ነበር።
ደብዳቤው ኩክ ቤት ለማግኘት ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀማቸውን ያትታል።
ደብዳቤው አክሎም ኩክ ሁለት ሐሰተኛ ሰነዶችን በሁለት ሳምንት ልዩነት በሁለት የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ቤቶች ቋሚ መኖሪያቸው መሆናቸውን በመግለጽ መፈረማቸውን ዘርዝሯል።
በእነዚህ ውንጀላዎች የተነሳ ኩክ ላይ ክስ ያልተመሰረተ ሲሆን ምርመራ ስለመደረጉም ይፋ የሆነ መረጃ የለም።
የኩክ ክስም እነዚህን ውንጀላዎች በቀጥታ አይጠቅስም።
ቀደም ሲል እርሳቸውን ከሥልጣን ለማባረር ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ አስተባብለው የነበረ ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች በትራምፕ አቋም ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል።
ኩክ ከሰባት የፌዴራል ሪዘርቭ የገዥዎች ቦርድ አባላት አንዷ ናቸው። ይህ ሥልጣናቸው አሜሪካ ውስጥ የወለድ ተመኖችን የማዘጋጀት ኃላፊነት ባለው 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሥልጣናቸውን ዳግም ከተረከቡ በኋላ በማዐዕከላዊ ባንክ ገዢዎች ላይ በተሌእ ደግሞ በፖውል ላይ የወለድ ምጣኔ ላይ ጭማሪ አንዲያደርጉ ቻና ማድረግ ቀጥለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለዚህ ሥልጣን እጩዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ስለዚህ ኩክ ከስልጣናቸው ሲባረሩ የወለድ ምጣኔን ለመቀነስ እና ለትራምፕ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ የበለጠ ምቹ የሆነ ሰው ይተካል ማለት ነው።
የፌዴራል ሪዘርቭ ውሳኔ አሜሪካውያን መበደር የሚችሉትን መጠን እና በቁጠባ ሒሳባቸው ላይ ያለውን የወለድ መጠን ይነካል።
የሌሎች አገራት ማዕከላዊ ባንኮች የአገራቸውን የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔ ሲያስቀምጡ የአሜሪካን የወለድ መጠን በቅርበት ይከታተላሉ።
ኩክ በሐምሌ ወር መጨረሻ በማዕከላዊ ባንኩ የመጨረሻ የዋጋ መተመኛ ስብሰባ ላይ የአሜሪካን የወለድ ተመኖችን ለማስጠበቅ ከፖውል እና ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ጋር በመሆን ድምጽ ሰጥተዋል ።















