ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፌደራል ግምጃ ቤት ገዥን ለማባረር አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፌደራል ግምጃ ቤት ገዥ የሆኑትን ሊሳ ኩል ከኃላፊነታቸው በአስቸኳይ እንደሚያነሱ ተናገሩ።
ይህም ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ጋር የገቡበት ትልቅ ግጭት መባባሱ አመላካች ሆኗል።
ትራምፕ 'ቱሩዝ ሲሻል' በተባለው የግላቸው የማኅበራዊ የትስስር ገፅ ይፋ ባደረጉት እና ለሊሳ ኩክ በተፃፈ ደብዳቤ በአስቸኳይ ከብሔራዊ ባንኩ ቦርድ አባልነታቸው እንዲነሱ የደረሱበትን ውሳኔ ይገልፃል።
ትራምፕ በቤት ግዢ የብድር ስምምነቶች ላይ የተሳሳተ መግለጫ ለማውጣታቸው አሳማኝ "በቂ ምክንያት" አለ ካሉ በኋላ፤ ገዥዋን ከኃላፊነታቸው ለማንሳት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት ኩክ ትራምፕ ከሥራቸው ለማባረር ምንም ሥልጣን የላቸውም፤ እኔም ሥራዬን አልለቅም ብለዋል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕጉ መሰረት ምክንያት ሲያጡ 'ምክንያት ፈጥረው' እንደሚያባርሩኝ ተናግረዋል። ይህን ለማድረግ ጨርሶ ምንም ሥልጣን የላቸውም" ሲሉ ባወጡት መግለጫ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ሥራዬን በገዛ ፈቃዴ አልለቅም። ከ2022 ጀምሮ ሳደርገው እንደነበረው የአሜሪካን ምጣኔ-ሀብት ለማገዝ ኃላፊነቴን መወጣቴን እቀጥላለሁ" ብለዋል።
የሊሳ ኩል ጠበቃ ኤብ ዴቪድ ሎውል "[የትራምፕን] እየሞከሩ ያሉትን ሕገ ወጥ እርምጃ ለመከላከል መወሰድ ያለበትን የትኛውንም እርምጃ ሁሉ እንወስዳለን" ብለዋል።
የፌደራል ግምጃ ቤት ትራምፕ ሠኞ ዕለት ይፋ ስላደረጉት ውሳኔ እስካሁን አስተያት አልሰጠም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግምጃ ቤቱ ላይ ጫናቸውን እያጠናከሩ ሲሆን፤ በተለይም በሊቀ መንበሩ ጅሮም ፓውል የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ባለፉት ሳምንታት ጫና እያደረጉባቸው ነው።
ትራምፕ ፓውልን የማባረር ሁኔታንም ደጋግመው አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሰባቱ የፌደራል ግምጃ ቤት የቦርድ ገዥዎች ውስጥ አንዷ እና በዚህ ኃላፊነት የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት የሆኑትን ሊሳ ኩክን ለማባረር ያሳለፉት ውሳኔ፤ በብሔራዊ ባንኩ 111 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሎ ይታመናል።
እርምጃው የሕግ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ሲሆን፤ ባለሙያዎች ዋይት ሐውስ ሊሳ ኩክን ለማባረር በቂ ምክንያት እንዳለው ለፍርድ ቤት ማሳመን ሳይኖርበት አይቀርም እያሉ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት በቤት ግዥ የብድር ስምምነት ማጭበርበር ክስ ምክንያት ሊሳ ኩክ የሥራ መልቀቂያ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ኩክ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ ስለ ማጭበርበር ክሱ ከመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ጠቁመው፤ የብድር ማመልከቻው ብሔራዊ ባንኩን ከመቀላቀላቸው በፊት የቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።
በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ምክንያት ኃላፊነቴን የመልቀቅ ምንም ፍላጎት የለኝም ብለዋል።
ሊሳ ኩክ አሊያም ግምጃ ቤቱ የትራምፕን የማባረር ውሳኔ የሚቃወሙ ከሆነ በዋይት ሐውስ እና በብሔራዊ ባንኩ መካከል ይፋዊ ፍጥጫ እንደሚፈጥር ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
የፌደራል ግምጃ ቤት እ.አ.አ በ1951 ከአሜሪካ መንግሥት ነፃነቱን ያገኘ ገለልተኛ ተቋም ነው።















