ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራዊው ቢንያም ግርማይ በቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ታሪክ አስመዘገበ
ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ በአለም ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን ቱር ደ ፍራንስ የተሰኘውን የፈረንሳዩን የብስክሌት ውድድር ‘ስቴጅ 3’ [ሶስተኛ ዙር] በማሸነፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ በመሆን ታሪክ ሠራ።
ቢንያምን ተከትለው ኮሎምቢያዊው ፈርናንዶ ጋቪሪያ እና ቤልጂየማዊው አርኖድ ዴ ሊ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።
ከውድድሩ በፊት ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ማርክ ካቬንዲሽ በግጭት ምክንያት እንደተጠበቀው ለድል ባይበቃም ውድድሩን ለማጠናቀቅ በቅቷል።
እስካሁን ባለው ውድድር በአጠቃላይ ሰዓት ለመምራት የቻለው ሪቻርድ ካራፓዝ ቢጫ መለያ በማጥለቅ የመጀመሪያው ኢኳዶራዊ ለመሆን በቅቷል። ታዴይ ፖጋካር እና ሬምኮ ኤቨንፖል በተመሳሳይ ሰዓት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኤርትራዊው ቢንያም በ 2022 በዢሮ ዲኢታሊያ የመጀመሪያውን ትልቅ ‘ስቴጅ’ በማሸነፍ በብስክሌት ውድድር ያለውን ስም ከፍ ማድረግ ችሎ ነበር።
"ሁሉንም ጥንካሬ እና ድጋፍ ስለሰጠኝ ስለ ሁሉም ነገር ፈጣሪ ይመስገን እላለሁ" ሲል ቢንያም ተናግሯል።
"ብስክሌት መንዳት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ላይ እወዳደራለሁ የሚል ህልም አልነበረኝም። አሁን የሆነውን ግን ማመን አልቻልኩም። ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ ኤርትራን እና አፍሪካን አመሰግናለሁ” ብሏል።
"መኩራት አለብን። አሁን በትልልቅ መድረኮች ከመሳተፍ ባለፈ ስኬትም አስመዝግበናል። አሁን የእኛ ጊዜ ነው፣ ይህ የእኛ ጊዜ ነው። ይህ ለመላው አፍሪካ ነው" ሲል “የአፍሪካ የብስክሌት ንጉሥ” ተብሎ የሚታወቀው ቢንያም ተናግሯል።
በተደጋጋሚ ውድድሩን በማሸነፍ የሚታወቀው ማርክ ካቬንዲሽ በውድድሩ መጠናቀቂያ አካባቢ በደረሰ ግጭት ለድል ባይበቃም ጉዳት ስላልደረሰበት ደስተኛ መሆኑን አስታውቋል።
ውድድሩ ዛሬም በመቀጠል ከፒኔሮሎ እስከ ቫሎየር 139.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ውድድር ይከናወናል።
ማክሰኞ ውድድሩ ከፒኔሮሎ ወደ ቫሎየር በተራራማው 139.6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኃያል ኮል ዱ ጋሊቢየር ሲጓዝ ውድድሩ ወደ ኧልፕስ ተራሮች ይሄዳል።
ቱር ደ ፍራንስ በተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የብስክሌት ግልቢያ ውድድር ነው።
በየዕለቱ የሚካሄደው ውድድር ‘ስቴጅ’ የሚባል ሲሆን በ23 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ብስክሌተኞች ለሁለት ቀናት ብቻ አርፈው ቀሪዎችን 21 ቀናት የሚወዳደሩበት አድካሚ እና ስመ ገናና ውድድር ነው።