በአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመዘጋታቸው በርካቶች ከሥራ እንደሚሰናበቱ ዋይት ሀውስ አስታወቀ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ ዓመታዊ የመንግሥት በጀት አለመጽደቁን ተከትሎ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ በርካታ የፌደራል ሠራተኞችን ከሥራ እንዲሰናበቱ ማድረግ እንደሚጀመር ዋይት ሀውስ አስታወቀ።

ኮንግረስ ውስጥ የሚገኙ ሪፐብሊካኖች እና ዲሞክራቶች እስከ ረቡዕ ሌሊት ድረስ በአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ላይ ሳይስማሙ በመቅረታቸው የተነሳ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ ማቆም ጀምረዋል።

በሁለቱም ወገኖች ያሉ የኮንግረስ አባላት አገሪቱ ከሰባት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እዚህ ሁኔታ ውስጥ ለመግባቷ አንዳቸው ሌላኛቸውን ይወነጅላሉ።

ሪፐብሊካኖችም ሆኑ ዲሞክራቶች እስካሁን ድረስ አቋማቸውን የመቀየር አዝማሚያ አላሳዩም።

በበጀት አለመጽደቅ ምክንያት የመጣውን የመንግሥት አገልግሎቶች መቋረጥ ለማስቆም በሚል ሲካሄድ የነበረው ድምጽ የመስጠት ሂደትም በተጀመረ በሰዓታት ውስጥ እንዲቆም ተደርጓል።

ይህንን ተከትሎም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥራ የሚመለሱበት ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል የተሰጋ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም የመባረር ስጋት ውስጥ ወድቀዋል። ሁኔታው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ ውስጥ እንደሚከትተውም ተፈርቷል።

የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቢዘጉም እንደ የድንበር ጥበቃ እና ወታደሮች ያሉ ወሳኝ ሠራተኞች ለጊዜው ያለ ክፍያ ሥራቸውን ያከናውናሉ። ወሳኝ ያልሆኑ ተብለው የሚመደቡ ሠራተኞች ደግሞ ያለ ክፍያ እረፍት እንዲወጡ ይደረጋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር በዚህ መልኩ እረፍት የወጡ ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲመለሱ ያለ ሥራ ያሳለፏቸው ቀናት ክፍያ ይፈጸምላቸዋል።

ተንታኞች የዘንድሮው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘጋት በአውሮፓውያኑ 2018 ከነበረው የባሰ ሊሆን እንደሚችል እየተናገሩ ነው። ከፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ውስጥ 40 በመቶው ወይም 750,000 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በጊዜያዊነት እረፍት እንዲወጡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከፕሬስ ሴክሬታሪዋ ካሮላይን ሌቪት ጋር በመሆን ረቡዕ ዕለት በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ገብተዋል ያሏቸውን ዲሞክራቶች ወቅሰዋል።

"ይህ ጉዳይ በአሜሪካ ሕዝብ ላይ ስለሚያመጣው ጉዳት ተጨንቀው ከሆነ፤መጨነቅም አለባቸው፤ ማድረግ ያለባቸው መንግሥቱን መልሶ ሥራ ማስጀመር እንጂ ምላሽ የምንሰጥበትን መንገድ ላይ ቅሬታ ማቅረብ አይደለም" ብለዋል።

ሌቪት በበኩላቸው፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ሠራተኞችን ማሰናበት እንደሚጀመር ገልጸዋል። የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ "አንዳንዴ ማድረግ የማትፈልጋቸውን ነገሮች ማድረግ አለብህ" በማለት ተናግረዋል።

"እዚህ ሁኔታ ውስጥ የከተቱን ዲሞክራቶች ናቸው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት ያሰሙት ወቀሳ እርስ በእርስ እየተካሰሱ ላሉት ሁለቱ ፓርቲዎች አዲስ አይደለም። ከዚህ አስቀድሞ በሴኔት የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር ሪፐብሊካኖች ዲሞክራቶች "በጉልበት" የበጀት ዕቅዱን እንዲቀበሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው በማለት ከስሰው ነበር።

ዲሞክራቶች በበጀት እቅዱ ላይ ከመስማማታቸው በፊት የጤና አገልግሎት ፕሮግራሞች ገንዘብ እንደሚመደብለት ማረጋገጫ ማግኘት ይፈልጋሉ።

የሪፐብሊካኖች ዕቅድ ደግሞ የአጭር ጊዜ በጀት በማቅረብ መሥሪያ ቤቶች ከዚህ ቀደም ያገኙት የነበረውን ገንዘብ እያስመደቡ እስከ ኅዳር አጋማሽ ድረስ የመንግሥት አገልግሎት እንዳይቆም ማድረግ ነው።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው የመንግሥት አገልግሎት እንዲቆም ያደረጉት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አሜሪካውያን የሚጠቀሙበት የጤና አገልግሎት የሚቀጥልበት መንገድ ላይ ለመደራደር እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሪፐብሊካኖች ጋር ያደረጉት ድርድር ግን እስካሁን ውጤት አለማምጣቱን ተናግረዋል።

ሪፐብሊካኖች በኮንግረስ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር ቢይዙም የበጀት እቅዱን ለማጽደቅ የሚያስችላቸው 60 ድምጽ የላቸውም። ሪፐብሊካኖች ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባቸው መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መክፈት እንጂ የጤና አግለግሎት ጉዳይ አይደለም በማለት ይሟገታሉ።