ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የቡርኪናፋሶ መሪ መፈንቅለ መንግሥት ተደረገባቸው
የቡርኪናፋሶ የጦር መኮንኖች በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ሌተናል ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳምቢባ ከሥልጣን መወገዳቸውን አስታወቁ።
የቡድኑ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ እንደተናገሩት የወታደራዊ መሪው ሌትናል ኮሎኔል ዳምቢባ ከመሪነት የተወገዱት፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱትን እስላማዊ አማጺያንን በአግባቡ መቆጣጠር አልቻሉም በሚል ነው።
መኮንኑ ጨምረውም ላልተወሰነ ጊዜ ሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች ዝግ እንደሚሆኑ እና የትኛውም አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መከልከሉን አሳውቀዋል።
አሁን ከሥልጣን መወገዳቸው የተገለጸው ዳምቢባ የሚመሩት ቡድን፣ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ነበር በሕዝብ የተመረጠውን አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት ገልብጦ ወደ ሥልጣን የመጣው።
በወቅቱም ወታደራዊ ቡድኑ መንግሥት የእስላማዊ ቡድኖችን ጥቃት ማስቆም አልቻለም በሚል ነበር መፈንቅለ መንግሥት ማድረጉን ያሳወቀው።
ትናንት አርብ ጠዋት ላይ በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ውስጥ ከባድ ተኩስ ከተሰማ በኋላ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ሌተናል ኮሎኔል ዳምቢባ ጠይቀው ነበር።
ትናንት ምሽት ላይ ከ20 በላይ የሚሆኑ አብዛኞቹ ፊታቸው የተሸፈነ የታጠቁ ወታደሮች በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የቡድኑ መሪ ናቸው በተባሉት ትራኦሬ የተፈረመ መግለጫ አቅርበዋል።
“እየተባባሰ የሚሄድ ችግር በገጠመን ጊዜ ዳምቢባ በደኅንነት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክረናል፤ ነገር ግን የዳምቢባ ተግባር ለማድረግ ካቀድነው ውጪ በመሆኑ አሁን ከሥልጣን እንዲወገድ ወስነናል” ብሏል መግለጫው።
ከዚህ በኋላም በመላዋ አገሪቱ ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 11 የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን፣ ሌተናል ኮሎኔል ዳምቢባ የት እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።
አሜሪካ ቡርኪናፋሶ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ነገር “በእጅጉ እንዳሳሰባት” በመግለጽ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎቿ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቆጥቡ መክራለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ “መረጋጋት እንዲሰፍንና ሁሉም ወገኖች ከየትኛውም ድርጊት እንዲቆጠቡ” ጥሪ አቅርበዋል።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበር የሆነው ኤኮዋስ “ሥልጣንን ሕገ መንግሥታዊ ከሆነ መንገድ ውጪ መያዝና በሥልጣን ላይ መቆየትን አጥብቄ እቃወማለሁ” በማለት በቡርኪናፋሶ የተካሄደውን የመንግሥት ግልበጣውን አውግዞታል።
አርብ ዕለት አጥቢያ በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት እና በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ውስጥ ባለ ጦር ሰፈር አቅራቢያ የተኩስ ድምጽና ፍንዳታ መጀመሪያ ላይ ተሰምቶ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ጠዋት ላይ ወታደሮች አንዳንድ መንገዶችን በመዝጋት ቁልፍ የከተማ ክፍሎች ላይ በመሰማራታቸው ለወትሮ ግርግር የሚበዛበት ከተማ ጭር ብሎ ነበረ።
ቀን ላይ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ሲሆን የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያም ስርጭቱን ለሰዓታት አቋርጦ ቆይቶ ነበር።
የመፈንቅለ መንግሥት ወሬ በስፋት በተናፈሰበት አርብ ከሰዓት በኋላ ፕሬዝዳንቱ ሌ/ኮሎኔል ዳምቢባ፣ በአንዳንድ ወታደሮች ዘንድ የተፈጠረ ስሜታዊነት “ግራ መጋባትን” መፍጠሩን በመግለጽ “ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ድርድር እየተካሄደ ነው” በማለት ሕዝቡ እንዲረጋጋ ጠይቀው ነበር።
አሁን ከሥልጣን መባረራቸው የተነገረው ዳምቢባ ባለፈው ዓመት ጥር ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬን እየጨረ የመጣውን የእስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃትን መቆጣጠር አልቻሉም በሚል ነበር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ያስወገዱት።
ነገር ግን ዳምቢባ ወደ ሥልጣን ከመጡም በኋላ በርካታ ዜጎች ደኅንነት እንደማይሰማቸው በመግለጽ በዚህ ሳምንት በተለያዩ የቡርኪናፋሶ ክፍሎች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
አርብ ከሰዓት በኋላ አንዳንዶች በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ውስጥ ሌተናል ኮሎኔል ዳምቢባ ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቅ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር።
በቡርኪናፋሶ የእስላማዊ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ከሰባት ዓመት በፊት የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሁለት ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።
ቡርኪናፋሶ በአውሮፓውያኑ 1960 ነጻ አገር ከሆነች በኋላ እስካሁን ድረስ ስምንት የተሳኩ መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂዶባታል።