ከፖል ፖግባ በግዳጅ ገንዘብ ለመውሰድ ሞክሯል የተባለው ታላቅ ወንድሙ ሶስት ዓመት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ ፖል ፖግባ ታላቅ ወንድም ከእግር ኳስ ኮከቡ በግዳጅ ገንዘብ ለመውሰድ በመሞከር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።
ማቲያስ ፖግባ ሶስት ዓመት የተፈረደበት ሲሆን አንድ ዓመት እስር ቤት አሳልፎ ሁለቱን ዓመት ደግሞ በሕግ ቁጥጥር ሥር ይሆናለእ።
በተጨማሪ የ20 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ቅጣት የተላለፈበት ማቲያስ ፖግባ ቅጣቱን መክፈል ከቻለ ከእስር የሚያመልጥ ቢሆንም ለአንድ ዓመት መቆጣጠሪያ ተገጥሞለት ይቆያል።
ሌሎች አምስት ሰዎች ገንዘብ በግዳጅ ለመውሰድ በሚሉ በሌሎች ወንጀለኞች ጥፋተኛ ተብለዋል።
ሐሙስ ዕለት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ የዋለው ችሎት ከአራት እስከ ስምንት ዓመት እስር በይኖባቸዋል።
የ31 ዓመቱ ፖል ፖግባ "በልጅነት ጓደኞቼ ነው የተታለልኩት" ብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2022 ነው ተከሳሾቹ ፖግባ ላይ ሽጉጥ ደግነው 13 ሚሊዮን ዩሮ ካልተሰጣቸው እንደማይለቁት አስታውቀው የነበረው። ፖግባ እንደሚለው ለተከሳሾቹ 100 ሺህ ዩሮ ከፍሏል።
የማቲያስ ፖግባ ጠበቃ ምቤኮ ታቡላ ውሳኔው "እጅግ ከባድ ነው" ሲሉ አርኤምሲ ስፖርት ለተሰኘው ጣቢያ የተናገሩ ሲሆን "ይግባኝ የምንጠይቅ ይመስለኛል" ሲሉ አክለዋል።
ሮሽዴን ኬ ስምንት ዓመት፣ ቡባካር ሲ 4 ዓመት፣ አዳም ሲ አምስት ዓመት፣ ማማዱ ኤም አምስት እንዲሁም ማቺኮር ኬ ተፈርዶባቸዋል።
ባለፈው ዓመት ፖል ፖግባ በአብሮ አደግ ጓደኞቹ በደረሰበት ወንጀል ምክንያት ጫማውን ለመስቀል እንዳሰበ ለአል-ጃዚራ ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል።
"ገንዘብ ሲኖርህ ልትጠነቀቅ ይገባል" ብሏል ፖግባ።
"ገንዘብ ሰዎችን ይቀይራል። ቤተሰብ ሊያቆራርጥ ይችላል። ጦርነት ሊፈጥር ይችላል።"
እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው ማቲያስ ፖግባ ለፓትሪክ ቲስትል፣ ሬክስሀም፣ ክሬው አሌክሳንድራ እና ክራውሊ ታውን ተጫውቷል። ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው ቤልፎርት ለተባለ የፈረንሳይ ክለብ ሲሆን በ2022 ነው ከክለቡ ጋር የተለያየው።












