ራሽፈርድ ማንቸስተር ዩናይትድን ጥሎ ይሄድ ይሆን? ማንስ ሊያስፈርመው ይችላል?

ማርከስ ራሽፈርድ እና አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ማርከስ ራሽፈርድ።

ለማንቸስተር ዩናይትድ 426 ጨዋታዎችን አድርጓል። በክለቡ የምን ጊዜ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ ላይ በ138 ጎሎች 12ኛ ነው።

የ27 ዓመቱ እንግሊዛዊ ከዩናይትድ ጋር ኤፍኤ ዋንጫ እና ኢኤፍኤል ዋንጫ በልቷል። የአውሮፓ ሊግንም አንስቷል። ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን 60 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ከሜዳ ውጭ ደግሞ ድኅነት ላይ ያሉ ሕፃናትን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት በአውሮፓውያኑ 2021 ኤምቢኢ የተሰኘ ክብር አግኝቷል።

ነገር ግን አሁን ከእናት ክለቡ ጋር ያለው ግንኙነት ደመና ያጠላበት ይመስላል። ምናልባትም ክለቡን ሊለቅ ይችላል የሚሉ ጭምጭምታዎች አሉ።

ባለፈው እሑድ በማንቸስተር ደርቢ በቡድኑ ውስጥ አለመካተቱ ሁኔታዎችን አባብሷል።

እንዴት እዚህ ሊደርስ ቻለ?

በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 18፤ 2023 ራሽፈርድ ከዩናይትድ ጋር ያለውን ውል አራዝሞ እስከ ሐምሌ 2028 እንደሚቆይ ክለቡ አስታወቀ።

ከክለቡ ጋር የነበረው ውል ሊጠናቀቅ 12 ወራት ሲቀሩት ነው ይህ የሆነው። በወቅቱ ታላላቅ ከሚባሉ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ነበር።

ውሉን ሲያራዝም ዕድሜው 25 ነበር። በእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ጨዋታዎች በ2022/23 የውድድር ዘመን 30 ጎሎች አስቆጥሯል።

ዩናይትድ በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን የውጤት ቀውስ ውስጥ ሲገባ ራሽፈርድ በ13 ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ተሳነው።

ባለፈው ጥር በኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ከኒውፖርት ካውንቲ ጋር በነበረው ጨዋታ ሳይሰለፍ ቀረ። ፈቃድ ጠይቆ ወደ ቤልፋስት ሄዷል ቢባልም መሸታ ቤት ሲገባ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጡ።

ቴን ሀግ ተሰናብተው ሩበን አሞሪም የዩናይትድ አሰልጣኝ ሆነው ተቀጠሩ። በመጀመሪያ ጨዋታቸው አንድ አቻ ሲወጡ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ራሽፈርድ ነው።

አሰልጣኙ ራሽፈርድ የመሐል አጥቂ ሆኖ መጫወት እንደማይሆነው አመኑ። በአዲሱ አሰልጣኝ ሥር ሶስት ጊዜ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ሲጫወት ሶስት ጊዜ ተቀይሮ ገብቷል።

ዩናይትድ ከአርሰናል እና ኖቲንግሀም ፎረስት ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሲረታ ራሽፈርድ ተቀይሮ ነው የገባው። በአውሮፓ ሊግ ከቪክቶሪያ ፕሌዘን በነበረው ጨዋታ ደግሞ በ56ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወጣ።

በማንቸስተር ደርቢ ዩናይትድ ሲቲን ሲረታ ማርከስ ራሽፈርድ እና አሌሀንድሮ ጋርናቾ በቡድኑ ውስጥ አልተካተቱም።

አሞሪም "ሁለቱ ተጫዋቾች በልምምድ ሥፍራ ጥሩ አቋም ስላልነበራቸው ነው ያልተመረጡት" የሚል አስተያት ሰጡ።

ማከርስ ራሽፈርድ በዩናይትድ ማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ራሽፍርድ ትችት የሚቀርብበት ለምንድነው?

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የዩናይትድ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ከተጫዋቾች ጋር መጋጨት አዲሳቸው አልነበረም። ከዴቪድ ቤካም እስከ ፖል ፖግባ ድረስ የነበረውን ማስታወስ ይቻላል።

አሞሪምለ፤ ራሽፈርድን በቡድናቸው ውስጥ ሳያካትቱ ሲቀሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያውቁታል።

ዩናይትድ በሲቲ ቢረታ ሁኔታዎች ምናልባትም ሌላ መልክ ይይዙ ነበር። ምክንያቱም ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው ብቸኛ አጥቂ ተጫዋች ጆሹዋ ዚርክዚ ነበር። ነገር ግን ምስጋና ለዲያሎ ይሁንና ዩናይትድ ከሜዳው ውጭ ያደረገውን ጨዋታ በድል ተወጣ።

"ተጫዋቾችን ብንቀንስም ማሸነፍ እንደምንችል አሳይተናል" ሲሉ አሞሪም ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ሰጡ።

ራሽፈርድ በ2022/23 የውድድር ዘመን ያሳውን ብቃት መድገም የቻለ አይመስልም። ብዙዎች ተጫዋቹ ምርጥ ብቃት እንዳለው ቢመሰክሩም በአንዳንድ ጨዋታዎች አቋሙ ተዳክሞ መታየቱ ምናልባትም ከክለቡ ጋር ያለው ጊዜ እያበቃ መጥቷል አስብሏል።

አንዳንድ ጊዜ ሜዳ ላይ በሚያሳየው የደከመ አቋም ሲተች ይስተዋላል። አንዳንዶች ደግሞ ከሜዳ ውጭ በሚያደርገው ድርጊት ይተቹታል። ባለፈው ኅዳር በነበረው የክለቦች እረፍት ወቅት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ማቅናቱ ትችት አስከትሎበት ነበር።

ከሌሎች የዩናይትድ ተጫዋቾች በተለይ ራሽፈርድ ትኩረት ይሰጠዋል የሚሉ አሉ። ነገር ግን ከትችት ሊያመልጥ አይችልም።

ራሽፍርድ ምን ሊያስፈርመው ይችላል?

ማርከስ ራሽፈርድ በማንቸስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፈላቸው ተጫዋቾች መካከል ነው። በሳምንት 300 ሺህ ፓውንድ ይከፈለዋል። ይህንን ደመወዝ መክፈል የሚችሉ ጥቂት ክለቦች ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ በራሽፈርድ ቦታ ተጫዋች ስላላቸው ሊያስፈርሙት አይችሉም።

የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ካለበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንፃር ራሽፈርድን ማስፈረም አይችልም። ሪያል ማድሪድ ደግሞ ኪሊያን ምባፔ፣ ቪኒሲየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሀም አሉት።

የፈረንሳዩ ግዙፍ ክለብ ፓሪ ሳን ዠርማ ከራሽፈርድ ጋር ብዙ ጊዜ ስሙ ይነሳል። ነገር ግን ክለቡ በይፋ ራሽፈርድን እንፈልገዋለን የሚል አስተያየት ሰጥቶ አያውቅም።

ምናልባት ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ ወደ ዩናይትድ መጥቶ ራሽፈርድ ወደ ፒኤስጂ ሊሄድ ይቻላል ቢባልም ራስመስ ሆይለንድ የአሞሪም ተመራጭ አጥቂ እየሆነ መጥቷል።

የሳዑዲ ሊግ ትልቅ ስም ያለውን የ27 ዓመቱን ራሽፈርድ ሊያስፈርም ይችላል ቢባልም ተጫዋቹ ግን ወደ ሳዑዲ አራቢያ የመሄድ ፍላጎት ያለው አይመስልም።

ምናልባት በሚመጣው ጥር በውሰት ሊሄድ ይችላል የሚለው ጭምጭምት ውሀ የሚያነሳ ይመስላል። ቢሆንም ዩናይትድ ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቻቸውን በራሳቸው ወጪ ለሌላ ክለብ አሳልፈው ይሰጣሉ የሚለው ስሜት አይሰጥም።

ራሽፈርድ በኦልድ ትራፈርድ ሊቆይ ይችላል?

ዌይን ሩኒ በአውሮፓውያኑ 2010 ዩናይትድ ለቆ ይሄዳል ተብሎ ወሬው ከተሰራጨ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አዲስ ውል መፈረሙ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን መገናኛ ብዙኃንን በክፉ ወቅሰው ነበር።

የሩኒ ታሪክ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት የማይቻል ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው።

ነገር ግን ራሽፈርድ በዩናይድት የሚቆይ ከሆነ ሶስት ነገሮች ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።

አንደኛ ተጫዋቹ አሞሪም የሚጠይቁትን ነገር ሟሟላት ይችላል ወይ? የሚለው ነው። የዚህ ጥያቄ ምላሽ ከባድ አይደለም። ተጫዋቹ ቋሚ ተሰላፊነቱን ለማረጋገጥ የበለጠ መጣር ይጠበቅበታል።

ሁለተኛው ደግሞ በአዲሱ አሰልጣኝ አሰላልፍ ውስጥ ቦታ አለው ወይ? ነው። ይህ ጉዳይ ትንሽ የተወሳሰብ ነው። ራሽፈርድ በግራ ክንፍ ተሰልፎ ወደ መሐል እየገባ መጫወትን ይመርጣል። የአሞሪም 'ስትራቴጂ' ደግሞ ለዚህ ቦታ የለውም። ነገር ግን ራስመስ ኳስ መቆጣጠር ከቻለ የራሽፈርድ ፍጥነት ለዩናይትድ ጠቃሚ ይሆናል።

የመጨረሻው ጉዳይ ልዩነት የሚፈጥር ተቀያሪ መሆን ነው። ራሽፍድ የእግር ኳስ ሕይወት ጫፍ ላይ ነው የሚገኘው። ተቀያሪ ሆኖ ማየት የሚከብድ ይሆናል።