ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያዊው የኦርቶዶክስ ካህን የስታሊንን አዲስ ሐውልት በመባረካቸው ምርመራ ተከፈተባቸው
አንድ የሩሲያ የኦርቶዶክስ ካህን የሶቪየት ኅብረት አምባገነን መሪ የነበረውን ጆሴፍ ስታሊንን አዲስ ሐውልት መባረካቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ምርመራ ተከፈተባቸው።
ክስተቱ የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ማክሰኞ እለት በቬሊኪዪ ሉኪ ከተማ የስምንት ሜትር ርዝመት ያለው የዚህ ሐውልት ምረቃ ላይ ነው።
የአካባቢው አገረ ስብከት የካህኑ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኗን አመለካከት አይወክልም የሚል መግለጫም አውጥቷል።
ከጎሮጎሳውያኑ 1924 እስከ 1953 ድረስ ሶቭየት ኅብረትን አንቀጥቅጦ የገዛው ስታሊን በአረመኔያዊ አገዛዝ ታሪክ የሚያነሳው ሲሆን ሃይማኖትንም ለማጥፋት ሞክሯል።
የሩሲያው ገለልተኛ የዜና ጣቢያ ሶታ እንደዘገበው ካህኑ በስታሊን አገዛዝ ዘመን በርካታ የሃይማኖት አባቶች መገደላቸውን አምነው ይህ ደግሞ ሰማዕታት እንዲኖሩ ማድረጉን ተናግረዋል።
ካህኑ የሚያገለግሉበት አገረ ስብከት በበኩሉ በዚህ የሐውልት ምረቃ ዝግጅት ላይ እንዲሳተፉ እንዳልተፈቀደላቸው እና “የውስጥ ምርመራ” መጀመሩን ገልጿል።
በስታሊን የሦስት አስርት ዓመታት አገዛዝ ውስጥ ከተገደሉት ወይም አስገዳጅ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ በግዞት ከተላኩት በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቀሳውስት እንደነበሩ ይገመታል።
ሃይማኖት ለስኬታማ የሶሻሊስት ማኅበረሰብ እንቅፋት ሆኖ በመታየቱ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል፣ ወይም በኃይል ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ተቀይረዋል።
የስታሊኒዝም ጽንሰ ሃሳብ በምስራቅ አውሮፓ የማይሽር ጠባሳ የተወ ሲሆን አሁንም በርካቶች በጭካኔው ያወግዙታል።
በሩሲያ ምድር ውስጥ ያሉ በርካታ የስታሊን ሐውልቶች እንዲወገዱ ተደርገዋል።
አሁን ለቆመው አዲስ ሐውልት ቦታ ለማግኘት ሦስት ዓመታት ፈጅቷል ሲልም የመንግሥት ሚዲያ የሆነው ሪያ ኖቮስቲ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በአንድ ወቅት ስታሊንግራድ ይባል የነበረው የቮልጎግራድ ከተማ ባለስልጣናት ሐውልቱ በከተማዋ እንዳይቆም በመቃወማቸው ይህንን ያህል ጊዜ መፍጀቱም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለ ስታሊን በጎ አመለካከት ያላቸው ሩሲያውያን ቁጥር እየጨመረ ነው።
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሌሎች ባለስልጣናት ቢሆኑም አገሪቱን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን ላይ ድል እንድትጎናጸፍ ያስቻሉ መሪ ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።