ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ እንዲባረሩ ትዕዛዝ ያስተላለፉባቸው የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ፕሬዝዳንቱ ላይ ክስ ሊመሰርቱ ነው
ፌደራል ሪዘርቭ ተብሎ ከሚጠራው የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ሰባት ገዢዎች መካከል አንዷ የሆኑት ሊሳ ኩክ፤ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሥልጣን መነሳታቸውን በመቃወም ክስ ሊመሰርቱ ነው።
ይህ እርምጃም ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ ማዕከላዊው ባንክ ጋር የገቡበት ትልቅ ግጭት መባባሱን የሚያመለክት ሆኗል።
ጠበቃዋ አቤ ዴቪድ ሎውል በሰጡት መግለጫ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፌደራል ሪዘርቭ ገዢ ሊሳ ኩክን ከኃላፊነት የማንሳት ሥልጣን የላቸውም" ብለዋል።
ትራምፕ በቤት ግዢ የብድር ስምምነቶች ላይ የተሳሳተ መግለጫ ለማውጣታቸው አሳማኝ የሆነ "በቂ ምክንያት" አለ ካሉ በኋላ፤ ገዥዋን ከኃላፊነታቸው ለማንሳት ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፌድ ሪዘርቭ ላይ ጫናቸውን እያጠናከሩ ሲሆን፤ በተለይም የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኛ ባልሆኑት ሊቀ መንበሩ ጅሮም ፓውል ላይ ባለፉት ሳምንታት ጫናቸውን እያሳደሩ ነው።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት ኩክ፤ ትራምፕ ከሥራዬ ለማባረር ምንም ሥልጣን የላቸውም፤ እኔም ሥራዬን አልለቅም ብለዋል።
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ የረዥም ጊዜ ቦንድ ዋጋ የቀነሰ ሲሆን ይህም ባለሀብቶቸ ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ያሳያል ተብሏል።
ትራምፕ የፌደራል ሪዘርቭ ገዢን፤ ለማባረር መሞከራቸው ባለሀብቶች በማዕከላዊ ባንኩ ላይ ያላቸውን እምነት ይሸረሽራል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ሰዎች የፌደራል መንግሥቱ ላይ ያላቸው እምነት ከቀነሰ የአሜሪካ መንግሥት ገንዘብ ለመበደር ሊቸገር ይችላል።
ይህም የአሜሪካ የብድር ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ዋጋዎችን ስለሚተምን የዓለም አቀፉ ገበያ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ኩክ ከሰባት የፌዴራል ሪዘርቭ የገዥዎች ቦርድ አባላት አንዷ ናቸው። ይህ ሥልጣናቸው አሜሪካ ውስጥ የወለድ ተመኖችን የማዘጋጀት ኃላፊነት ባለው 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል።
የኩክ ጠበቃ ማክሰኞ ዕለት "በቀረበ አንድ አቤቱታ ላይ በመመስረት ብቻ እሷን ለማባረር ያደረጉት ሙከራ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ወይም ሕጋዊ መሠረት የለውም" ብለዋል።
"ይህን ሕገወጥ ድርጊት በመቃወም ክስ እንመሰርታለን" ሲሉም አክለዋል።
የፌደራል ሪዘርቭም አስተያየቱን ሰጥቷል።
"ኮንግረስ በፌዴራል ሪዘርቭ ሕግ መሠረት ገዥዎች ለረጅም ጊዜ በቋሚነት እንዲያገለግሉ መመሪያ ይሰጣል፤ [ገዥዎቹ] በፕሬዚዳንቱ ሊነሱ የሚችሉት 'በምክንያት' ብቻ ነው" ሲል ማዕከላዊ ባንኩ በመግለጫው ላይ ገልጿል።
"ለገዥዎች የረዥም ጊዜ ቆይታ እና ያለመነሳት ጥበቃ [መሰጠቱ] የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎች በመረጃ፣ በኢኮኖሚ ትንተና እና በአሜሪካ ሕዝብ የረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን በማረጋገጥ እንደ ወሳኝ ጥበቃ ያገለግላል።"
ኩክ በትራምፕ ላይ ለማቅረብ ያቀዱት ክስን ተከትሎ ባንኩ የፍርድ ቤት ውሳኔን እንደሚያከብር ተናግሯል።
ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኩክን ለመተካት ብዙ "ጥሩ ሰዎች" በአእምሯቸው ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ፤ "ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሆኑ ሰዎች እንፈልጋለን፤ እሷ የሆነች አይመስልም" ሲሉ በካቢኔ ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለዚህ ሚና እጩዎችን አቅርበዋል፣ ስለዚህ ኩክ ከስልጣናቸው ሲባረሩ የወለድ ምጣኔን ለመቀነስ እና ለትራምፕ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ የበለጠ ምቹ የሆነ ሰው ይተካል ማለት ነው።
የፌዴራል ሪዘርቭ ውሳኔ አሜሪካውያን መበደር የሚችሉትን መጠን እና በቁጠባ ሒሳባቸው ላይ ያለውን የወለድ መጠን ይነካል።
የሌሎች አገራት ማዕከላዊ ባንኮች የአገራቸውን የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔ ሲያስቀምጡ የአሜሪካን የወለድ መጠን በቅርበት ይከታተላሉ።
ኩክ በሐምሌ ወር መጨረሻ በማዕከላዊ ባንኩ የመጨረሻ የዋጋ መተመኛ ስብሰባ ላይ የአሜሪካን የወለድ ተመኖችን ለማስጠበቅ ከፖውል እና ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ጋር በመሆን ድምጽ ሰጥተዋል ።
እአአ በ2022 ከትራምፕ በፊት በነበሩት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን የተሾሙ ሲሆን በዚህ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊ ሴት ናቸው።
ትራምፕ እርሳቸውን ከሥልጣን ለማባረር የወሰዱት ውሳኔ የሕግ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል።
ባለሞያዎቹ ዋይት ሐውስ እርሳቸውን ለማባረር በቂ ምክንያት እንዳለው ማሳየት እንዳለበት ይጠቁማሉ ።
ኩክ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕጉ መሰረት ምክንያት ሲያጡ 'ምክንያት ፈጥረው' እንደሚያባርሩኝ ተናግረዋል። ይህን ለማድረግ ጨርሶ ምንም ሥልጣን የላቸውም" ሲሉ ባወጡት መግለጫ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ሥራዬን በገዛ ፈቃዴ አልለቅም። ከ2022 ጀምሮ ሳደርገው እንደነበረው የአሜሪካን ምጣኔ-ሀብት ለማገዝ ኃላፊነቴን መወጣቴን እቀጥላለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት በቤት ግዥ የብድር ስምምነት ማጭበርበር ክስ ምክንያት ሊሳ ኩክ የሥራ መልቀቂያ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ኩክ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ ስለ ማጭበርበር ክሱ ከመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ጠቁመው፤ የብድር ማመልከቻው ማዕከላዊ ባንኩን ከመቀላቀላቸው በፊት የቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።
በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ምክንያት ኃላፊነቴን የመልቀቅ ምንም ፍላጎት የለኝም ብለዋል።
ሊሳ ኩክ አሊያም ፌደራል ሪዘርቭ የትራምፕን የማባረር ውሳኔ የሚቃወሙ ከሆነ በዋይት ሐውስ እና በማዕከላዊ ባንኩ መካከል ይፋዊ ፍጥጫ እንደሚፈጥር ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
የፌደራል ሪዘርቭ እ.አ.አ በ1951 ከአሜሪካ መንግሥት ነፃነቱን ያገኘ ገለልተኛ ተቋም ነው።