የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ግድያ የተቃወሙት አፍሪካ አገራት የትኛዎቹ ናቸው?
የፎቶው ባለመብት, Islamic Movement of Nigeria (IMN)
አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተከትሎ የአፍሪካ አገራት የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግሥታት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እና ሌሎችም ከኢራን ጋር ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ያላቸው ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ኢራን ለዓመታት በአፍሪካ አገራት በሚገኙ የሃይማኖት እና የባህል ተቋማት ላይ ኢንቨስት አድርጋለች። ነጻ የትምህርት ዕድሎችም ሰጥታለች።
ከኢራን ጋር ጥብቅ ትስስር ካላቸው አገራት መካከል ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ጋና እና ጋምቢያ ይጠቀሳሉ።
የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የናይጄሪያ እና ኒጀር ተቃውሞ
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሺአ ሙስሊሞች የሚኖሩባት ናይጄሪያ ለጠቅላይ መሪው ግድያ ቀድመው ምላሽ ከሰጡ አገራት አንዷ ናት።
በደቡብ ናይጄሪያ 12 ግዛቶች ውስጥ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፤ በኻሜኒ ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽ በርካቶች አደባባይ ወጥተዋል።
ማንኛውም ዓይነት አለመረጋጋት ወይም ግጭት እንዳይነሳ በሚል የፀጥታ ኃይሎች መሰማራቸው ተገልጿል።
ታዋቂ የሸአ ሙስሊሞች መሪ እና 'አልሚዛን' የተባለ የሃይማኖት መጽሔት አርታኢ ኢብራሒም ሙሳ እንደሚለው፤ ኻሜኒ "የሃይማኖት፣ የሞራል እና መንፈሳዊ አቅጣጫ ጠቋሚ" ተደርገው ይወሰዱ ነበር።
አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአስተምህሮታቸው እንደሚታወቁ ተናግሯል።
ናይጄሪያዊው የሺአ አክቲቪስት ፕሮፌሰር ኢሳህ ማሽልግሩ፤ የኻሜኒ ግድያ "በጣም የሚያሳምም ነው" ብለዋል። "በጣም ነው የምንናፍቃቸው። የሞተው ክብሩን ጠብቆ ስለሆነ እንኮራበታለን" ሲሉም ተናግረዋል።
አይኤምኤን የተባለ ኢስላማዊ ንቅናቄ መሥራች ኢብራሒም ዛከሪ፤ ከአውሮፓውያኑ 1979 ወዲህ ናይጄሪያውያን ሺአ ሙስሊሞች ከኢራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
በዋሽንግተን ኢንስቲትዩት የቀድሞ ወታደራዊ ባለሙያ እና በቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ኦማር ካርሚ እንደሚለው፤ የናይጄሪያ የሺአ ሙስሊም ንቅናቄ ኢራን በምዕራብ አፍሪካ ከምታደርገው እንቅስቃሴ ጉልህ የሚባለው ነው።
እንደ ናይጄሪያ ሁሉ በኒጀርም ሰልፎች ተካሂደዋል። በመዲናዋ ኒማይ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የኻሜኒን ግድያ በጽኑ አውግዘው ለኢራን ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
የናይጄሪያ እና ኒጀር መንግሥታት በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።
የሺአ ሙስሊሞች በሚኖሩባት ሌላዋ አፍሪካዊት አገር ጋምቢያ የሚኖሩት ዶ/ር ሱፊ አቲፍ አሚን አል ሑሴኒ "ኻሜኒ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ትክክለኛ መሪ ነበሩ" ብለዋል።
ኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት "የሞራል እና ሕግጋት መላሸቅ" ብለውታል። አሜሪካ እና እስራኤል "በዲፕሎማሲ እና ሞራል ከስረዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የቡርኪና ፋሶ እና ሴኔጋል ምላሽ
በቀጣናው ይፋዊ አቋም ከያዙ አገራት በዋናነት የምትጠቀሰው ቡርኪና ፋሶ ናት።
በኢራን ላይ የደረሰውን ጥቃት ያወገዘው የቡርኪና ፋሶ መንግሥት በመዲናዋ ኦጋዶጉ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ዘግቷል።
ይህ ውሳኔ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥን ያሳያል።
ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ከምዕራባውያን አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ጀምረዋል።
የኻሜኒ ግድያ ሉዓላዊነት እና የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጓል።
ሴኔጋል ስለ ኻሜኒ ግድያ ይፋዊ አቋማቸውን ካሳወቁ አገራት መካከል ስትሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማን ሶንኮ "እጅግ አስቀያሚ" ብለው ኮንነዋል።
"በመካከለኛው ምሥራቅ በአሜሪካ እና በአጋሯ እስራኤል ምክንያት ጦርነት ተነስቷል። ኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ወስነዋል። አገራትን ማጥቃት እና አፍኖ መቆጣጠር በጣም አሳፋሪ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ፈቃድ ያልሰጣት አገር ሌላን አገር ስታጠቃ እና ግድያ ስትፈጽም እጅግ ያሳስባል" ሲሉም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ሴኔጋል ከምዕራባውያን አገራትም ሆነ ከሙስሊሙ ዓለም ጋር ትስስር ነበራት። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከምዕራባውያን ጎን እንደማትቆም የሚጠቁም መግለጫ አውጥታለች።
ደበብ አፍሪካ እና ኬንያ ምን አሉ?
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያደረሱትን ጥቃት አውግዘዋል። ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ መሆኑን ገልጸዋል።
"ገና ለገና ጥቃት ሊደርስብኝ ይችላል ብሎ ጥቃት መፈጸምን ዓለም አቀፍ ሕግ አይፈቅድም። በግምት እና ቅድመ ግምገማ ጥቃት አይፈጸምም" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በባሕረ ሰላጤ አገራት ላይ የደረሰውን ጥቃት ኮንነዋል።
"በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ፣ ኦማን፣ ኩዌት፣ ዮርዳኖች እና ባሕሬን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ኬንያ ታወግዛለች" በማለት ተናግረዋል።
ጦርነቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መስፋፋቱ ዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋትን እንደሚያናጋም አስጠንቅቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ኢራን ያለችበት የብሪክስ አባል አገር ናት።
የአፍሪካ አገራት በይፋ ጥቃቶችን በማውገዝ አቋማቸውን እየገለጹ ነው። በተለይም በሰሀል አካባቢ ለሚገኙ አገራት የኢራን ጠቅላይ መሪ መገደል ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም