አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከእስር እስከ ስደት፣ ከአብዮተኝነት እስከ መሪነት

በአውሮፓውያኑ 1979 የተካሄደውን የኢራን እስላማዊ አብዮት ተከትሎ ላለፉት 45 ዓመታት በላይ የኢራን መንግሥት ዋነኛ ሥልጣንን ተቆጣጥረው የቆዩት ኤያቶላህ የሚባሉት መንፈሳዊ ጠቅላይ መሪዎች ሁለት ብቻ ናቸው።
አብዮቱን ተከትሎ ወደ መሪነት የመጡት አያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒ በሥልጣን መንበሩ ላይ የቆዩት ለ10 ዓመታት ሲሆን፣ የእሳቸውን ሞት ተከትሎ ከ35 ዓመታት በላይ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሆነው በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የቆዩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸው ተነግሯል።
እስራኤል ከምድረ ገጽ እንድጠፋ ይፈልጋሉ ስትል ምትከሳቸውን ኻሜኒን ለማጥመድ ለአስርታት ስታደባ ቆይታለች።
የእስራኤል የስለላ ተቋማት ኢራን ውስጥ ከታዋቂ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች አንስቶ ወደታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሥልጣናትን እዲሁም በጥብቅ ሲጠበቅ የነበረውን የሐማስ መሪን ኢስማኤል ሃኒዬን ጨምሮ ኢራን ውስጥ መግደል ችለዋል።
ጠቅላይ መሪውን ግን በቀላሉ ዒላማ ሊያደርጓቸው ሳይችሉ ቆይተዋል። ቅዳሜ ጠዋት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ቴህራን በሚገኘው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ መኖሪያ ላይ በፈጸመችው ከባድ ጥቃት መገደላቸው ተረጋግጧል።
የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ የነበሩት የ86 ዓመቱ አዛውንቱ መሪ ማን ነበሩ? በኢራን አብዮት እና በጠቅላይ መሪነቱ ውስጥ ምን ሚና ነበራቸው? ከየትስ ተነስተው ከኢራን ጠቅላይ መሪነት ላይ ደረሱ?

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/Shutterstock
አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እ.አ.አ. በ1979 ከተካሄደው የኢራን አብዮት በኋላ ሁለተኛው የሀገሪቱ የበላይ መሪ ሲሆኑ ከ1989 ጀምሮ በበላይ መሪነት ስፍራ ላይ ይገኛሉ። ወጣት ኢራናውያን ያለእርሳቸው አመራር ሕይወትን አያውቋትም።
ኻሜኒ ሽኩቻ በበዛበት የኃይል ማዕከል ላይ ተቀምጠዋል። ማንኛውንም የሕዝብ ፖሊሲ ጉዳይ ውድቅ ማድረግ እንዲሁም መሾም እና የመሻር ወሳኝ ሥልጣን አላቸው።
ኻሜኒ የኃያሉ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድን የሚያጠቃልል ጦር ኃይል ዋና አዛዥ እና የአገሪቱ መሪ እንደመሆናቸው ሥልጣናቸው ቀላል አይደለም።
ኻሜኒ በአውሮፓውያኑ 1939 በኢራን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ማሽሃድ ነው የተወለዱት።
በሃይማኖተኛ ቤተሰብ ውስጥ ከተወለዱት ስምንት ልጆች መካከል ሁለተኛ ልጅ የሆኑት የኻሜኒ አባት በኢራን ዋነኛው የእስልምና ቅርንጫፍ የሆነው የሺዓ እስልምና በመካከለኛ ደረጃ የነበሩ የሃይማኖት መምህር ነበሩ።
የሕጻኑ ኻሜኒ አብዛኛው የትምህርት ጊዜ ቁርዓንን በማጥናት የተሸፈነ ነበር። በ11 ዓመታቸውም የሃይማኖት መምህር ለመሆን በቅተዋል።
ነገር ግን በጊዜው እንደነበሩት ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ ሥራው ከመንፈሳዊ ባልተናነሰ መልኩ ፖለቲካዊም ነበር።
አንደበተ ርቱዕ የነበሩት ኻሜኒ በኢራን እስላማዊ አብዮት ከሥልጣን የተወገዱት የኢራን ንጉሥ ሻህ ተቺዎችን ተቀላቀሉ።
ለዓመታት በህቡዕ ወይም በእስር ቤት አሳልፈዋል። ከስድስት ጊዜ በላይ በኢራን ንጉሣዊ የምሥጢር ፖሊስ ተይዘው ለስቅይት እና አካባቢያቸውን ትተው እንዲሰደዱ ተደርገዋል።
በአውሮፓውያኑ 1979 የኢራን እስላማዊ አብዮት ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ አያቶላህ ሩሆላህ ኻሜኒ የዋና ከተማይቱ ቴህራን የጁምዓ ሶላት መሪ አድርገው ሾሟቸው።
በ1989 ደግሞ ኻሜኒ በ86 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አያቶላ ኾሜኒ ምትክ ሆነው በሃይማኖት መሪዎች ከመመረጣቸው በፊት በ1981 ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

የፎቶው ባለመብት, khamenei.ir
የአራት ወንድ ልጆቻቸው ሚና
አሊ ኻሜኒ ብዙም ከኢራን የማይወጡ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ቴህራን በሚገኝ ግቢ ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር የተቆጠበ ሕይወት ይመራሉ።
አትክልት መንከባከብ እና ሥነ ግጥም እንደሚያስደስታቸው ይነገራል። በኢራን ለሃይማኖት ሰው ባልተለመደ መልኩ በለጋ ዕድሜያቸው ሲጋራ ያጨሱ ነበር። በ1980ዎቹ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ የቀኝ እጃቸውን መጠቀም አይችሉም።
ኻሜኒ ከባለቤታቸው ማንሱሬ ኾጃስቴህ ባቄርዛዴህ አራት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች ልጆች በጥቅሉ ስድስት ልጆች አሏቸው ።
የኻሜኒ ቤተሰብ በአደባባይም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን እምብዛም አይታይም፣ ስለዚህም ስለ ልጆቻው የግል ሕይወት ያለው የተረጋገጠ እና ይፋዊ መረጃ ውስን ነው።
ከአራቱ ልጆቹ መካከል፣ ሁለተኛው ሞጅታባ በይበልጥ የሚታወቀው በአባቱ ዙሪያ ባሉ ባለሥልጣናት ላይ ባለው ጉልህ ተጽእኖ እና ሚና ምክንያት ነው።
ሞጅታባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በተለምዶ የእስላማዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልጆች በሚማሩበት እና በቴህራን በሚገኘው በአላቪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
የሃይማኖት መምር ባልሆነበት እና ቆም ውስጥ በሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሃይማኖት ትምህርት ለመጀመር ባቀደበት ወቅት ጎላም-አሊ ሃዳድ-አደል የተባለ ታዋቂ የወግ አጥባቂ ግለሰብ ሴት ልጅ ጋር ትዳር መሥርቷል።
ከዚያም በ30 ዓመቱ መደበኛ የሃይማኖት ጥናቶችን በኢራን ውስጥ በጣም ታዋቂ በሆነው በቆም የሺዓ እስልምና መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ጀምሯል።
ምንም እንኳን በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ብዙም ትኩረትን ባያገኝም በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ አጋማሽ ላይ ሞጅታባ በፖለቲካው መስክ ያለው ተጽእኖ የበለጠ ግልጽ ሆኗል።
ሞጅታባ በ2004 ከተካሄደው አጨቃጫቂ ፕሬዝንታዊ ምርጫ ትኩረትን አግኝቶ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ታዋቂው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ መህዲ ካሩቢ ለአያቶላ ኻሜኒ በጻፉት ደብዳቤ ማህሙድ አህመዲነጃድን ለመደገፍ ከመጋረጃው ጀርባ ጣልቃ ገብቷል በሚል ክስ ስለቀረበበት ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮም በእስላማዊው ሪፐብሊክ ውስጥ ካሉት በጣም ኃያላን ግለሰቦች መካከል አንዱ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም የኻሜኒ ተተኪ ለመሆን ተመራጭ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል። አንዳንድ ኦፊሴላዊ ምንጮች ግን እነዚህን መላምቶች ውድቅ አድርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, khamenei.ir
አሊ ኻሜኔ ንጉሥ ባለመሆናቸው ዙፋናቸውን ለልጃቸው በቀላሉ ማስተላለፍ ባይችሉም፣ ሞጅታባ በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ አካላት ላይ የበላይነት ባለው እና ከፍተኛ ሥልጣንን በያዘው የጠቅላይ መሪውን ቢሮን ጨምሮ አክራሪ በሆኑት በአባቱ ዙሪያ ባለሥልጣናት ውስጥ ሳይቀር ከፍተኛ ተሰሚነት አለው።
ሙስጠፋ ኻሜኒ የቤተሰቡ ደግሞ የአሊ ኻሜኒ የበኩር ልጅ ነው። ሚስቱ አክራሪ ወግ አጥባቂ የሃይማኖት መሪ የሆኑት የአዚዞላህ ሖሽቫግት ልጅ ነች።
በ1980ዎቹ የኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት ሁለቱም ሙስጠፋ እና ሞጅታባ በጦር ግንባር ተሰልፈው ነበር።
ሦስተኛው የአሊ ኻሜኒ ልጅ መስዑድ የሚባል ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1972 ነው የተወለደው። ከቆም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ወግ አጥባቂ የመምህራን ማኅበር ጋር ግንኙነት ያለው ታዋቂው የሃይማኖት መምህር ሞህሳን ኻራዚ ሴት ልጅ ሱዛን ኻራዚ ጋር ትዳር መሥርቷል።
መስዑድ ኻሜኒ ፖለቲካ በደረሰበት የማይደረስ ሲሆን፣ በሕዝቡ ዘንድ ስለ እሱ ብዙም በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።
ቀደም ሲል የአባቱን ሥራዎች የሚቆጣጠረውን እና ለአያቶላ ኻሜኒ ቁልፍ የፕሮፓጋንዳ ክንድ ሆኖ የሚሠራውን ቢሮ ይመራ ነበር። የአባቱን የሕይወት ታሪክ እና የግል ማስታወሻዎችን የማጠናቀር ኃላፊነትም ነበረው።
የቤተሰቡ ትንሹ ወንድ ልጅ መይሳም የተወለደው በ1977 ነው። እንደ ሦስት ታላላቅ ወንድሞቹ እሱም የሃይማኖት መምህር ነው።
ባለቤቱ ስሟ በመገናኛ ብዙኃን ተጠቅሶ የማያውቅ ሲሆን፣ ከ1979 አብዮት በፊት አብዮታዊ የሃይማኖት መምህራንን በገንዘብ በመደገፍ የሚታወቀው ሀብታም እና ተደማጭነት ያለው ነጋዴ የማህሙድ ሎላቺያን ልጅ ነች።
መይሳም ከወንድሙ መስዑድ ጋር የአባታቸውን ሥራዎች በማሰባሰብ እና በማሳተም ሥራ ውስጥ ተሳትፏል።
የአያቶላህ ሁለት ሴት ልጆች
ስለ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሴት ልጆች እምብዛም በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።
ሴት ልጆቻቸው ቡሽራ እና ሁዳ በዕድሜ ትንሾቹ የቤተሰቡ አባላት ሲሆኑ፣ ሁለቱም የተወለዱት ከ1979 አብዮት በኋላ ነው።
ቡሽራ የተወለደችው እ.ኤ.አ. በ1980 ሲሆን የኻሜኒ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆነው የጎላምሆሴን መሐመድ ጎልፓዬጋኒ ልጅ የሆነውን መሐመድ-ጃቫድ መሐመዲ ጎልፓዬጋኒን አግብታለች።
የመሪው መጨረሻ ልጅ የሆነችው እና በ1981 የተወለደችው ሆዳ፤ በኢማም ሳዲቅ ዩኒቨርሲቲ ያስተምር ከነበረው የማርኬቲንግ ምሩቅ መስባህ አል ሆዳ ባገሪ ካኒ ጋር ትዳር መስርታለች።















