በኬንያ ከኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የሚሰረቅ መርዛማ ዘይት ለምግብ ማብሰያነት እየተሸጠ ነው ተባለ

ኤሌክትሪክ እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Kenya Power

የኬንያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ድርጅት ከሃይል ማስተላላፊያ ወይም ትራንስፎረመር ላይ እየተሰረቀ እንደ ማብሰያ ዘይት የሚሸጠው ፈሳሽ መሰረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት በማድረስ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ኪሳራ እያስከተለ እንደሆነ ገለጸ።

የኬንያ ኤሌክትሪክ ሃይል ወንጀለኞች ፈሳሹን ከትራንስፎርመሮቹ ውስጥ በማውጣት ለሬስቶራንቶች እና በመንገድ ዳር ምግብ ለሚያዘጋጁ በሽያጭ ቀርቦ ምግብ ለማብሰል እና ለመጥበስ እንደሚሸጥ አስታውቋል።

ከምግብ ዘይት ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ይህ ድርጊት አንዳንድ የንግድ ድርጅቶችን እነዚህ የሚዘረፉ ዘይቶችን መግዛትን ጨምሮ ወዳልተለመዱ የምግብ ማብሳያ አማራጮች እንዲሄዱ አድርጓቸዋል።

የምግብ ዘይት የሚመስለው እና በትራንስፎርመር ውስጥ የሚገኘው ፈሳሸ ለሰው ልጅ ጤና አደጋ የሆነ እና ከፍተኛ የጤና ጠንቅ የሚያስከትል መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ሌሎች ወንጀለኞች ደግሞ የግለሰቦች ወይም የንግዶች ተቋማትን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በማቋረጥ መልሶ ለመቀጠል ገንዘብ ይጠይቃሉ።

በኬንያ 20 የሚጠጉ ትራንስፎርመሮች እንደወደሙ ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በማዕከላዊ ኬንያ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን የኬንያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታውቋል።

በኬንያ ቢያንስ 22 ሰዎች ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

እየተፈጸሙ ባሉ ስርቆቶች ምክንያት ከፍተኛ የሃይል መቆራረጥ የገጠመው የኬንያ ኤሌክትሪክ ሃይል አሁኑ ላይ የሃይል መሰረተ ልማቶችን ማውደም ስለሚያስከትለው አደጋ በአገር አቀፍ ደረጃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ጀምሯል።

ከወራት በፊት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙ ዝርፊያዎች በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የሃይል መቆራረጥ አስከትሏል።