ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በዋስ ተፈታ

የፎቶው ባለመብት, Terara Network ተራራኔትዎርክ
የተራራ ኔትወርክ መስራችና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ በዛሬው ዕለት መጋቢት 28፣ 2014 ዓ.ም በ50 ሺህ ብር ዋስ ከእስር መለቀቁን ባለቤቱ ሰላም በላይ እንዲሁም ተቋሙ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት መጋቢት 27፣ 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጋዜጠኛው በዋስ እንዲለቀቅ የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎም ከ118 ቀናት የእስር ቆይታ በኋላም ተፈትቷል።
ፍርድ ቤቱ ከመጋቢት 2፣ 2014 ዓ.ም ጀምሮም የጋዜጠኛውን የዋስ መብት ጥያቄ ሲመረምር እንደነበር ባለቤቱ ሰላም ለቢቢሲ ገልጻለች።
አያያዙንም በተመለከተ ከእስረኞቹ የተለየ ነገር እንዳልነበረው የተናገሩችው ባለቤቱ አሁንም በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል ብላለች።
"ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ወደቤት መምጣት ቀላል ነገር አይደለም። ያለፈበት ነገር ቀላል ባይሆንም፤ ለምን እንደታሰረ ሳይታወቅ በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ሳይወነጀል ይህንን ያህል ጊዜ ታስሮ መቆየቱ ቀላል ጉዳይ አይደለም።በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ወደቤቱ መምጣት መቻሉ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን"ብላለች
ጋዜጠኛው እስካሁን ድረስ ክስ እንዳልተመሰረተበትና መጋቢት 1፣ 2014 ዓ.ም በገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅትም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ጋዜጠኛው ላይ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
የታምራት ጠበቃ መጋቢት 2፣ 2014 ዓ.ም በዋስ እንዲለቀቅ የዋስ መዝገብ የከፈቱ ሲሆን ከተለዋዋጭ ቀጠሮዎችም በኋላ ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት ጋዜጠኛው በዋስ እንዲወጣ ብያኔ ሰጥቷል።
የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ እንዲሁም ከስደት መልስ ተራራ ኔትወርክ የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ሲሰራ የቆየው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰደው ታህሳስ 01፣ 2014 ዓ.ም ነበር።
በወቅቱም ሶስተኛ ፓሊስ ጣቢያ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ የተወሰደ ሲሆን በገላን ፖሊስ ጣቢያ እና ዳለቲ ማረሚያ ቤትም ከሶስት ወራት በላይ በእስር ቆይቷል።
ታምራት ነገራ ከአስር ዓመት በፊት በህትመት ላይ ቆይታ ከፍተኛ ዝና አትርፋ በነበረችው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመጻፍ ይታወቅ የነበረ ሲሆን፣ ጋዜጣዋ በመንግሥት ጫና ስትዘጋ ታምራትን ጨምሮ አብዛኞቹ የአዲስ ነገር ባልደረቦች ለስደት መዳረጋቸው ይታወሳል።
ታምራት ነገራ ለዓመታት በአሜሪካ በስደት ከቆየ በኋላ በአገሪቱ ከሦስት ዓመት በፊት የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ባለፈው ዓመት ተራራ ኔትወርክ የተባለውን የዩቲብ መድረክ በመጀመር የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች ሲያቀርብ ቆይቷል።












