ታማሚዎች ለሕክምና ወደ ሕንድ የሚጎርፉት ለምንድን ነው?

ቺሊያዊው ሁዋን ፍራንሲስኮ ፓላዲንስ ነገሮች ሁለት ሆነው ይታዩት ሲጀምሩ የሆነ ችግር እንደተፈጠረ አወቀ።

በሚኖርበት አገር ቺሊ፣ ክትትል የሚያደርጉለት ሐኪሞች ነገሮች ሁለት ሆነው የሚታዩትና ሌሎችም ምልክቶቹ በጭንቅላቱ ውስጥ እጢ እያደገ ስለመሆኑ እንደሚጠቁሙ ነገሩት።

ሁዋን ምልክቶቹን ማየት የጀመረው ከአስር ዓመታት በፊት ነበር።

"በሕይወቴ በጣም አስቸጋሪው ጊዜ ነበር። ደግነቱ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና የማውቃቸው ሰዎች በሙሉ በጣም ነበር የሚረዱኝ። ሁሉም ከጎኔ ነበሩ'' ይላል በቺሊዋ ሳንቲያጎ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ56 ዓመቱ ሁዋን።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደነገሩት ከሆነ አንጎሉ ውስጥ ያደገው እጢ በቅርጹ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን በራዲዬሽን ሕክምና ቀስ በቀስ የሁዋን ምልክቶች መጥፋት ጀመሩ።

ለቀጣዮቹ አራት ዓመታትም የጭንቅላት እጢው ማደጉን አቆመ። "ሁሉም ነገር የተስተካከለ መሰለኝ። ከነጭራሹ ስለ እጢው ማሰብም አቆምኩኝ" ይላል።

ነገር ግን በ2019 እኤአ ነገሮች ሁለት ሆነው የሚታዩት ምልክት ተመልሶ መጣ። በዚህም ምክንያት ከራዲዬሽን ህክምና በተጨማሪ ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ ጀመረ።

በቅርብ ዓመታት 'ፕሮቶም ቢም ቴራፒ' የተሰኘ አዲስ አይነት የካንሰር ሕክምና ተጀምሯል። ይህ ሕክምና ቀላል ኃይልን በመጠቀም የካንሰር እጢዎችን ዒላማ በማድረግ የማጥፋት ሂደት ነው።

የፕሮቶን ጨረሮች ሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ በቀላሉ እጢዎችን ማጥፋት የሚችል ውጤታማ የሕክምና አይነት ነው።

በዚህ ምክንያት ጭንቅላት ውስጥ፣ አንገት አካባቢ እንዲሁም የጀርባ አጥንት ላይ ለሚካሄዱ የጨረር ሕክምናዎች ተመራጭ ነው።

የሁዋን ሐኪም ለእሱ የሚሆነው ሕክምና ይሄኛው እንደሆነ ነገሩት። ነገር ግን ይህ ሕክምና በቺሊም ሆነ በጎረቤት አገራት አልነበረም።

"በመላው ዓለም ስለሚገኙ ሆስፒታሎችና ሕክምናውን በተመለከተ በጣም ሰፊ ጥናት አካሄድኩኝ። የትኛው ሆስፒታል የፕሮቲን ቴራፒ ሕክምና እንደሚሰጥና ዋጋቸውንም አጣራሁ።"

አብዛኛዎቹ አማራጮች በጣም ውድ እንዲሁም ለጉዞ የማይመቹ ሆኑበት። ነገር ግን በስተመጨረሻ ሕንድ ውስጥ የሚገኘውን አፖሎ ሆስፒታል አገኘ።

"እጅግ በጣም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ነው የሚጠቀመው። በተጨማሪ ደግሞ ዋጋው በጣም ተመጣጣኝ ነበር። በምዕራቡ ዓለም ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አለው።''

ይሄው ሆስፒታል ሁዋን ሕክምናውን ለመከታተል ሲሄድ ማረፊያ ቦታ እንዲያገኝ ያመቻቸለት ሲሆን የመጓጓዣ ሂደቱም ላይ ተባብሮታል።

ሁዋን በየዓመቱ ለሕክምና ብለው ወደ ህንድ ከሚጓዙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

ከ2016 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ለሕክምና ወደ ሕንድ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከ430 ሺህ ወደ 700 ሺ ከፍ ብሏል። በዚህም የተነሳ የሕንድ የሕክምና ኢንዱስትሪ በ2019 ላይ አጠቃላይ ገቢው 9 ቢሊየን ዶላር ደርሶ ነበር።

ነገር ግን የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ይህ ዘርፍ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

የሕንድ ቱሪዝም ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት 2021 ላይ 183 ሺ ሕክምና ፈላጊዎች ወደ ሕንድ ገብተዋል። ይህ ደግሞ 2019 ላይ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ73 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ከሕንድ በተጨማሪ እንደ ታይላንድ፣ ሲንጋፖር እና ማሌዢያ ያሉ ሌሎች የእሲያ አገራትም በሕክምና ቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገቡ አገራት ናቸው።

"በደቡባዊ እሲያ ሕንድ ከፍተኛውን የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ትይዛለች'' ይላሉ በአፖሎ ሆስፒታል የኦንኮሎጂ ባለሙያና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ዲኔሼ ማድሃቫን።

"አገራችን ያላት የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ከዘመናዊና ባህላዊ ሕክምና ጋር ተዳምሮ ለሕንድ ትልቅ እድል ፈጥሮላታል''

ወደ ሕንድ የሚሄዱት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ሕክምና ፈላጊዎች ሁሉም የካንሰር ታማሚዎች አይደሉም። ከሰውነታቸው ውስጥ ያለውን አላስፈላጊ ስብ ለመስወገድ የሚፈልጉ ሰዎች አንዳንዴም የጸጉር ንቅለ ተከላ የሚፈልጉም ይሄዳሉ።

"ታካሚዎች ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ባህረ ሰላጤው አገራት ድረስ ይመጣሉ። ሁሉንም አይነት ሕክምና እንሰጣለን'' ይላሉ የቆዳ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሳቲሽ ባቲያ።

ዶክተር ባቲያ እንደሚሉት ሕንድ ያለው የኮስሜቲክ ሕክምና ዋጋ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ሲነጻጸር 50 በመቶ ቅናሽ አለው። የህክምናው ጥራትና የምንጠቀመው ዘመናዊ መሳሪያም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ ነው ይላሉ።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የሕንድ የሕክምና ቱሪዝም አሁን ላይ እያንሰራራ ይመስላል። በሌላ በኩል ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚሁ ምክንያት ብቻ ብለው መምጣታቸው አሉታዊ ተጽዕኖም አለው።

''በመላው ሕንድ ውስጥ የውበት ክሊኒኮች በጣም እየተበራከቱ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ አካሄድ ደግሞ እውቀቱም ሆነ ፈቃዱ የሌላቸው ሐኪሞች በድፍረት እንዲገቡበት ያደርጋል። ቀላል ገንዘብ ማግኛ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ እና ያለአግባብ ሊነገድበት ይችላል'' ሲሉ ያስረዳሉ ዶክተር ሳቲሽ ባቲያ።

የሕንድ መንግሥትም ቢሆን ይህ ዘርፍ ትልቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው ያምናል።

"የሕንድ የሕክምና ቱሪዝም ዘርፍ በጣም ጠበቅ ያለ ቁጥጥር አይደረግበትም። ይህ ደግሞ ላልተፈለጉ ጉዳቶች ሊያጋልጥና ዘርፉንም ሊያዳክመው ይችላል'' የሚሉት ደግሞ በሕንድ ቱሪዝም ሚኒስቴር ምክትል ጸሐፊ የሆኑት ራኬሽ ኩማር ቨርማ ናቸው።

የሕንድ ዶክተሮች በጣም ከባድ በሆነ የስልጠና ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ የሚደረግ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ፈቃድ ለማግኘት በርካታ መመዘኛዎችን ማሟላት አለባቸው። ነገር ግን ችግሩ ያለው ዶክተሮቹ ጋር ሳይሆን ሕክምና ፈላጊዎችን ከሆስፒታል ጋር የሚያገናኙት ሰዎች ናቸው።

እነዚህ ሰዎች ልክ እንደ አስጎብኚዎች ሊቆጠሩ ይችላሉ። ዋነኛ ስራቸው ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ ሕክምና ፈላጊዎችን ከሚሆናቸው ሆስፒታል ጋር ማገናኘት ነው።

በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ደግሞ በበቂ ሁኔታ ስልጠና አለማግኘታቸውና በተገቢው መንገድ አለመደራጀታቸው ወደፊት ትልቅ ችግር ሊፈጥር ይችላል።