"የዓለም አስር ባለ ጸጎች ሀብት ቢደመር ለሁላችንም ክትባት ይገዛል"

ጄፍ ቤዞስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኦክስፋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በወረርሽኙ ወቅት ሀብታቸው የናረ አስር ወንዶች ሀብት ንብረት ሲደመር 540 በሊዮን ዶላር ይጠጋል።

ይህ ሀብት የዓለም ሕዝቦችን ከድህነት የሚያወጣ እንዲሁም ለሁሉም ሰው ክትበት መግዛት የሚያስችል እንደሆነ የተራድኦ ድርጅቱ ኦክስፋም ጠቁሟል።

በዓለም ላይ ያሉ ቢሊየነሮች ጠቅላላ ሀብት፤ የጂ-20 አገራት ወረርሽኙ ካሳደረው ጫና ለመላቀቅ ከሚያወጡት ወጪ እኩል መሆኑ በኦክፋም ሪፖርት ተመልክቷል።

ኦክስፋም ይህንን ሪፖርት ተመርኩዞ መንግሥታት ባለ ጸጎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲጥሉ ያሳስባል።

'ኢንኢኳሊቲ ቫይረስ' የተሰኘው ሪፖርት የወጣው መንግሥታት ለዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ጉባኤ በተሰበሰቡበት ወቅት ነው።

መንግሥታት ለምጣኔ ሀብታቸው ያደረጉት ድጋፍ የአክስዮን ገበያ እንዲያንሰራራና የቢልየነሮች ገቢ እንዲጨምር አድርጓል። የእነዚህ ግለሰቦች ሀብት ሲጨምር የአገራት ጠቅላላ ምጣኔ ሀብት ግን አሽቆልቁሏል።

ከሚያዝያ 2020 እስከ ጥቅምት 2020 የመላው ዓለም የቢልየነሮች ሀብት በ3.9 ትሪሊዮን ጨምሯል። የጂ-20 አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ያወጡት ወጪ ሲደመርም ከባለ ጸጎቹ ሀብት ጋር እኩል ነው።

በወረርሽኙ ወቅት ሀብታቸው ከናረ መካከል የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ የተስላ መስራች ኤለን መስክ እና የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ ይገኙበታል።

ጄፍ ቤዞስ ካለው ሀብት ለእያንዳንዱ 876,000 የአማዞን ተቀጣሪ 105,000 ዶላር ጉርሻ ቢሰጥ እንኳን ከወረርሽኙ በፊት የነበረው ሀብቱ እንደማይቀንስ ሪፖርቱ ያሳያል።

በተቃራኒው በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ወረርሽኙ ከሳደረባቸው ተጽዕኖ ለማገገም አስርት ዓመታት ያስፈልጋቸዋል።

በወረርሽኙ ሳቢያ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ድህንት አረንቋ እንደገቡ ኦክስፋም ገልጿል።

የኦክስፋም እንግሊዝ ዋና ኃላፊ ዳኒ ስሪስካንዳርጃህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ "ሀብታሞች ላይ ግብር በመጣል፣ ለእያንዳንዱ ዜጋ መሠረታዊ የገቢ መነሻ በማበጀትና በሌሎችም መንገዶች ፍትሐዊ ክፍፍልን ማረጋገጥ አለብን።"

በወረርሽኙ ወቅት አንዳንድ ሀብታም ሰዎች የገንዘብ ድጎማ እየሰጡ ነው።

የጄፍ ቤዞስ የቀድሞ ባለቤት መከንዚ ስኮት ያደረገችው የአራት ቢሊዮን ዶላር ድጎማ ይጠቀሳል።ጄ ፍ ቤዞስ ደግሞ ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚደረገውን ትግል ለመደገፍ 125 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል።

የትዊተር አጋር መስራች ጃክ ዶርሲ ከሀብቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲውል ሰጥቷል።

ቢል ጌትስ እና ባለቤታቸው መሊንዳ ለክትባት ምርትና ግዢ 305 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።