የቻይናና ሕንድ የድንበር ግጭት አገረሸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና እና የሕንድ ወታደሮች ዳግም ድንበር ላይ ተጋጩ፡፡
የሕንድ ሚዲያዎች እንደዘገቡት በግጭቱ የሞቱ የሕንድ ወታደሮች ባይኖሩም ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ወታደሮች ግን አሉ፡፡
ግጭቱ የተከሰተው ሕንድና ቻይና በሚዋሰኑበት የሰሜን ሲኪም አካባቢ ሲሆን ወታደሮቹ የተጋጩት ከሦስት ቀናት በፊት ነው፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ድንበር አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት መፈጠር የጀመረው ባለፈው ዓመት ወታደሮቻቸው ተጋጭተው ሞት ከተመዘገበ በኋላ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በጋልዋን ሸለቆ፣ ላዳክግ ግዛት በትንሹ 20 የሚሆኑ የሕንድ ወታደሮች በቻይና ወታደሮች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡
ከሦስት ቀናት በፊት ያገረሸው ግጭት ግን በሲኪም ናኩ ላ ድንበር አካባቢ ነው፡፡
ግጭቱ ያገረሸው አንድ ቅኝት የሚያደርግ የቻይና ወታደሮች ተሸከርካሪ በአካባቢው ድንበር አልፎ ሊገባ ሲል የሕንድ ወታደሮች ሊያስቆሙት ሲሞክሩ ነው፡፡
ለጊዜው በጉዳዩ ዙርያ የቻይም ሆነ የሕንድ ባለሥልጣናት ያሉት ነገር የለም፡፡
ይህ ስኪም ግዛት በቡታንና በኔፓል ድንበሮች ታጥሮ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡
ሕንድና ቻይና በዓለም ካሉ አገራት ሁሉ እጅግ ረዥሙን ድንበር የሚጋሩ ተጎራባቾች ናቸው፡፡
ሁለቱም አገራት ድንበር አካባቢ ያሉ ሰፋፊ ቦታዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄን ያነሳሉ፡፡ የይገባኛል ጥያቄዎች የሚነሱባቸው ቦታዎችም በጣም ብዙ ናቸው፡፡
ወንዞች፣ ኃይቆች እና በበረዶ ግግር የተሸፈኑ የተራራ ሰንሰለቶች ያሉባቸው እጅግ ውስብስብ የመልከአ ምድር አቀማመጥ ያሉባቸው አካባቢዎች በዚህ ሁለቱን ግዙፍ አገራትን በሚያጎራብቱ አካባቢዎች ስለሚገኙ ግልጽ ድንበር ለመለየት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡
ቻይናና ሕንድ የሚጋሩት ድንበር ርቀት 3ሺ 440 ኪሎ ሜትር ያህል ይረዝማል፡፡
በዚህ ረዥምና ውስብስብ ድንበር የተነሳ ሁለቱ አገራት ብዙውን ጊዜ የድንበር ወታደሮቻቸው ፊት ለፊት እየተገናኙ ይጋጫሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ሁለቱ አገራት ወታደሮቻቸው ግጭት ውስጥ ሲገቡ የጦር መሣሪያ አልተጠቀሙም፡፡
ከዚያ ይልቅ የጨበጣ ድብድብና ድንጋይ በመወራወር ነው 20 የሕንድ ወታደሮች ሊሞቱ የቻሉት፡፡
እነዚህ 20 የሕንድ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ ሁለቱ ኃያል አገራት ወደለየለት ግጭት እንዳይገቡ ተሰግቶ ነበር፡፡
በኋላ ላይ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ንግግር በመጀመራቸው ሁኔታዎች ሊቀለበሱ ችለዋል፡፤
ከዓለም ሕዝብ ብዛት 1ኛ እና 2ኛ የሆኑት ቻይናና ሕንድ ወደ ግጭት ቢገቡ ሁለቱም አገራት በንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ትስስር የፈጠሩ በመሆናቸው ለሁለቱም ጉዳት እንደሆነ የአካባቢው ምጣኔ ሀብት አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
ሕንድና ቻይና በዘመናዊ ታሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ከፍተኛ ጦርነት አድርገው ያውቃሉ፡፡
ይህም እንደ አውሮጳዊያኑ በ1962 ያደረጉት ሲሆን ሕንድ በከፍተኛ ጉዳት ከጦርነቱ ተሸናፊ ሆና ወጥታለች፡፡












