ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮና ቫይረስ፡ ስቲቪ ወንደር፣ ጆን ሌጀንድ፣ ሌዲ ጋጋ፣ በርና ቦይ... የጤና ባለሙያዎችን ያወደሱበት የቤት ኮንሰርት
በዓለማችን ውስጥ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው አርቲስቶች ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ኮሮናን እየተጋፈጡ ያሉትን የጤና ባለሙያዎች ለማሰብ ከቤታቸው ሆነው የሙዚቃ ኮንሰርት አካሂደዋል።
ከሙዚቀኞቹም መካከል ስቲቪ ወንደር፣ ሌዲ ጋጋ፣ ጆን ሌጀንድ፣ ጄኔፈር ሎፔዝ፣ በርና ቦይ፣ ፓውል ማካርቲና በአጠቃላይ 100 የሚሆኑ ሙዚቀኞች ከቤታቸው ሆነው ዘፍነዋል።
የሮሊንግ ስቶን ባንድ አባላትም አራት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሆነው በአንድ ላይ መጫወት ችለዋል።
ለስምንት ሰአታት ያህል በቆየው በዚህ ኮንሰርት የኮሮናቫይረስ ህሙማንን በሚያክሙና ድጋፍ በሚሰጡ ሰራተኞች አንደበት እውነተኛ ታሪኮች ተሰምተዋል።
ኮንሰርቱን በማዘጋጀት ትልቅ ስፍራ የነበራት ሌዲ ጋጋ " ይሄ ለዓለም የፍቅር ደብዳቤ ነው" ብላለች።
አክላም የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ድጋፍ ሰጪ አካላት ለዓለም ብዙ እያበረከቱ ነው "እናም ላሳያችሁን ደግነትን በትንሹም ለመመለስ ነው" ብላለች።
ፖል ማካርቲንም ቢሆንም የጤና ባለሙያዎቹን እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን " እውነተኛ ጀግኖች" በማለት ያሞካሻቸው ሲሆን፤ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ነርስ የነበረችውን እናቱንም በዚህ ወቅት አስታውሷታል።
"ዋን ወርልድ ቱጌዘር አት ሆም" (One World: Together At Home) የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ኮንሰርት የተዘጋጀው በግሎባል ሲትዝን ሙቭመንትና በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አማካኝነት ነው።
ሃገራት የቤት መቀመጥ አዋጅ ባወጁበት ሰአት ቤተሰቦቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና የሚወዷቸውን ሰዎች እንዲሁም ለህይወታቸው ሳይሳሱ ክፉኛ በቫይረሱ በተጎዱ እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ አሜሪካና በመሳሰሉት አገራት ያሉ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎች ፎቶዎች ታይተዋል።
"ፊት ለፊት እየተጋፈጣችሁ ያላችሁ የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ድጋፍ ሰጪዎች አብረናችሁ ነን። ስለረዳችሁን፣ ከጎናችን ስለቆማችሁ እናመሰግናለን" የሚልም መልእክት ተላልፏል።
ከሙዚቃ ዝግጅቱ የተገኘው ገንዘብ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ኮቪድ 19ን ለመታገል ለሚያደርገው ድጋፍ ይውላል ቢባልም ሌዲ ጋጋ በበኩሏ ይህ የእርዳታ ማሰባሰቢያ አይደለም። ትኩረቱም ማዝናናትና የትብብር መልእክቶች የሚተላለፉበት ብቻ ነው ብላለች።
ከነዚህም ሙዚቀኞች በተጨማሪ የዋን ዳይሬክሽኑ ኒያል ሆራን "ምንም እንኳን የጨለመ ቢሆንም መተባበርም የሰፈነበት ነው የሚል መልእክት አስተላልፏል።
ጆን ሌጀንድም ከሳም ስሚዝ ጋር በመጣመር 'የቤን ኢ ኪንግ' ስራ የሆነውን 'ስታንድ ባይ ሚን' አቀንቅነዋል።
የእንግሊዟ ዘፋኝ ሪታ ኦራ "አይ ዊል ኔቨር ሌት ዩ ዳውን' የሚለውን ዘፈን ከመዝፈኗ በፊት የዓለም አቀፍ ጤና ድርጅትን ምክር ህዝቡ እንዲሰማ መልእክቷን አስተላልፋለች።
አኒ ሊኖክስ በበኩሏ ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት የሚለግሱትን ገንዘብ አቆማለሁ ማለታቸውን በተመለከተ "ወቅቱ ዓለም ተባብሮ ይህንን ወረርሽኝ የሚያጠፋበት ወቅት እንጂ የምንበታተንበት ጊዜ አይደለም" ብላለች።
ኮንሰርቱ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ስድስት ሰአት በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ትዊተር፣ ዩ ቲዩብ በቀጥታ የተላለፉ ሲሆን የሁለት ሰአቱ የሙዚቃ ዝግጅት ደግሞ በሶስቱ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በስቴፈን ኮልበርት፣ ጂሚ ኪሜልና ጂሚ ፋለን በሚያዘጋጇቸው ዝግጅቶች ላይ የተወሰነው ክፍል ኮንሰርት ቀርቧል። ጂሚ ፋለንም ከሂፕሆፕ ቡድን ዘ ሩትስና የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችን በመጋበዝ በ80ዎቹ ታዋቂ የነበረውን ዳንስ አብረው ደንሰዋል።
ስቲቪ ወንደር፣ ጄኔፈር ሎፔዝ፣ በርና ቦይ፣ ሉይስ ፎንዚ፣ ሆዚየር በጥምረት ሆነው በቅርቡ ህይወቱ ያጣውን የቢል ዊዘር ዘፈን 'ሊን ኦን ሚን' ተጫውተዋል።
ቴይለር ስዊፍትም እናቷ በካንሰር ታመው እያለ ሆስፒታል ተቀምጦ መጠበቅ ያለውን ተስፋ አስቆራጭ ስሜት የገለፀችበትን "ዩ ዊል ጌት ቤተር' ኮሮና ቫይረስ የታመሙባቸው ቤተሰቦችን በመዘከር ተጫውታለች።
የኮንሰርቱም ማጠናቀቂያ የነበረው ጆን ሌጀንድ፣ ሴሊንድዮን፣ አንድሪያ ቦሴሊ በመጣመር በፀሎትና በዜማ ያቀነቀኑት ዘፈን ነው። ይሄ ፀሎት የተወሰደው በጎርጎሳውያኑ 1998 ለተሰራው ካሜሎት ፊልም ላይ ሲሆን መልእክቱም ከጨለማ መውጣትን የሚማፀን ነው።