የሌዎናርዶ ዳ ቪንቺ ውጥንቅጥ፡ የመጀመሪያዋ ሞና ሊዛ ማን ይሆን የሳላት?

ጊዜው 1960 ገደማ ነው። ሎንዶን ውስጥ የሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ግድግዳ ላይ አንድ ስዕል ተሰቅሏል። ይህ ስዕል ከኋላው ብዙ ጥያቄዎች አዝሏል። ስዕሉ የሞና ሊዛ ነው። ሰዓሊው ዳ ቪንቺ ይሆን? ስዕሉስ? 'ቀደምቷ' ሞና ሊዛ ትሆን?

አዎ ሰዓሊው ሌዎናርዶ ዳ ቪንቺ ነው፤ ብለው የሚያምኑ በርካቶች ናቸው። ከ50 ዓመታት በኋላ የስዕሉ ባለቤት ማን ይሆን? ሰዓሊውስ? የሚሉት ጥያቄዎች አከራካሪ ሆነዋል።

'ቀደምቷ ሞና ሊዛ' የተሰኘ ስም የተሰጠው ይህ ስዕል እውነተኛ ነው? ባለቤቱስ? እርግጥም የዳ ቪንቺ ሥራ ሆኖ ከተገኘ መቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ የጥብብ ሥራ ይሆን?

ይህንና መሰል ጥያቄዎችን ሊመልስ ይችላል የተባለለት የፍርድ ሂደት በዚህ ሳምንት ጣልያን ውስጥ ተጀምሯል።

ሁለተኛዋ ሞና ሊዛ?

በግሪጎሪያውያን አቆጣጠር 2012 ላይ የሞና ሊዛ ፋውንዴሽን የተሰኘ አንድ ድርጅት ሁለተኛዋ ሞና ሊዛ ብሎ የሰየመውን ስዕል ለሕዝብ ይፋ አደረገ።

'ሞና ሊዛ' የዓለማችን ታዋቂዋ ስዕል የሚል ቅፅላ ተሰጥቷታል። ሌዎናርዶ ዳ ቪንቺም ታላቁ ሰዓሊ የሚል ስያሜ የተሰጠው ጥበበኛ ነው። ታዲያ 'ቀደምቷ ሞና ሊዛ' እርግጥም የዳ ቪንቺ ሆና ብትገኝ ታሪክ መመሰቃቀሉ ነው።

'ፋውንዴሽኑ' ስዕሉን የኔ አይደለም፤ ባለቤቱን ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለሁም ቢልም እመኑኝ ሰዓሊው ዳ ቪንቺ ነው የሚል መከራከሪያ ይዞ ብቅ ብሏል።

የሎንዶን ከተማ ነዋሪዎቹ አንድሪው እና ካረን ጂልበርት ግን የስዕሉ 25 በመቶ ድርሻ የእኛ ነው ይላሉ።

ድርጅቱ 'ቀደምቷ ሞና ሊዛ' ብሎ ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግ ባልና ሚስቱ ስልክ መቱ። እነሱ እንደሚሉት ድርጅቱ ይሄኔ ፊት ነሳቸው። እኛ ባለቤቱን አናውቅም የሚል ምላሽ ነበር ከስልኩ ወዲያኛ ጫፍ ያገኙት።

ካረን እንዲህ ትላለች፤ «የስዕሉ ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ ማወቅ ስላልቻልን። ምን ማድረግ እንዳለብን አላወቅንም ነበር።»

ይህ ሳምንት ግን ለካረን እና አንድሪው ቀና ይመስላል።

450 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው ስዕል

ሳልቫቶር ሙንዲ ወይን የዓለም መድሃኒት [መድሃኒ ዓለም] የተሰኘው ስዕል ተመሳሳይ ታሪክ አለው።

ይህ የጥበብ ውጤት 1958 [በግሪጎሪያውያን አቆጣጠር] በ45 ዩሮ ተሸጠ። በአሁኑ ምንዛሬ ገበያ 1700 ብር ገደማ መሆኑ ነው።

የዛሬ ሁለት ዓመት ግን ለጨረታ እንዲቀርብ ሆነ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ገዢ ስዕሉን በ450 ሚሊዮን ዶላር የግላቸው አደረጉት። ዓለም ጉድ አለ።

የሌዎናርዶን ታሪክ የመዘገበው ጣልያናዊው ጄዎርጆ ቫሳሪ ዳ ቪንቺ ሞና ሊዛን ለመሳል አራት ዓመት እንደፈጀበትና መጨረሻ ላይ ሳያጠናቅቅ እንደተዋት ፅፏል።

'ቀደምቷ ሞና ሊዛ' ጀርባዋ ሲጠና አንድ ያልተጠናቀቀ ቅርፅ እንዳላት መረዳት ይቻላል ይላሉ ስዕሉን ተዟዙረው መጎብኘት የቻሉ ባለሙያዎች። የፈረንሳዩ ሉቭረ ሙዚዬም ውስጥ በኩራት ተሰቅላ ከምትገኘው ትክክለኛዋ ሞና ሊዛ የሚለያትም ይህ ነው ባይ ናቸው።

አልፎም ሌዎናርዶ ሞና ሊዛን ለሁለት ደንበኞቹ ሊስል ተዘጋጅቶ እንደነበር መዛግብት ይጠቁማሉ። ይህ ማለት ሁለት ሞና ሊዛዎች ቢኖሩ የማያስደንቅ ማሳያ ነው ሲሉ መከራከሪያቸውን ያስቀምጣሉ።

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዢን-ፒየር ኢስቦትስ ስዕሉ እውነተኛ ለመሆኑ ሶስት ማስረገጫዎች ያስቀምጣሉ። አንደኛ ስዕሉ በ16ተኛው ክፍለ ዘመን የተሳለ መሆኑ፤ ሁለተኛ የስዕሉ አቀራረፅ ሙዚየም ከምትገኘው ሞና ሊዛ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ፤ ሶስተኛ ደግሞ በሁለቱም ስዕሎች ላይ ያለው የእጅ ቅብ አጣጣል የዳ ቪንቺ ለመሆኑ ለእውነተኛነቱ ማስረገጫዎች ናቸው ይላሉ።

ይህ ፅንሰ-ሃሳብ ግን ሁሉን የሚያስማማ ሆኖ አልተገኘም። ከተቺዎች መካከል ደግሞ ፕሮፌሰር ማርቲን ኬምፕ አንዱ ናቸው። ሁሉም የዳ ቪንቺ ሥራዎች በብዙ ሂደት ውስጥ ያለፉ ናቸው፤ ስለዚህ ሁለተኛው ስዕል ሊሆን ይችላል የሚለው አመክንዮ ውሃ አያነሳም ይላሉ።

ስዕሉ እነ ጂልበርት እጅ እንዴት ገባ?

እስከ 1913 ድረስ ስዕሉ በማን እጅ እንደነበር የሚያሳይ መዝገብ የለም። 1913 ላይ ሂዩ በሌከር የተባለ ሰው እጅ ላይ ነበር። እርሱ ሲሞት ሄንሪ ፑሊትዘር የተሰኘ የጥበብ ሥራዎች ደለላ እጅ ሥር ተገኘ። የጂልበርት ቤተሰቦች ፑሊትዘር ያውቁት ነበር። ስዕሉን የገዙት እነሱ ናቸው ይላል ጂልበርት። ታድያ ሙሉ ስዕሉን ሳይሆን 2 መቶውን ድርሻ ነበር የሸመቱት።

ፑሊትዘር ከመሞቱ በፊት ስዕሉን ስዊተዘርላንድ የሚገኝ ባንክ ውስጥ ካለ ካዝና ውስጥ አኑሮት ነበር። ከዚያ በኋላ ስዕሉ የታየው 2008 ላይ ነው።

የሞና ሊዛ ፋውንዴሽን ሰዎች ከላይ ባለው የጂልበርት ታሪክ አይስማሙም።

ይሄኔ ነው አንድሪውና እና ካረን ጂልበርት አዋጭው መንገድ ሕግ ነው በማለት ወደ ክስ ያመሩት። አሁን ላይ 'ቀደምቷ ሞና ሊዛ' የጣልያኗ ፍሎረንስ ከተማ ውስጥ ለሕዝብ ዕይታ ቀርባለች። የፍርድ ሂደቱም ጣልያን ውስጥ ነው እየታየ ያለው።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ካስተዋለ በኋላ ቀጣዩን የፍርድ ውሎ ለወርሃ መጋቢት ቀጥሯል።