በአልቢኖ ግድያ የተሳተፉ ሦስት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው የ155 ዓመት እስራት ተበየነባቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አልቢኖ ያለበትን ግለሰብ የገደሉ ሦስት ሰዎችን እያንዳንዳቸውን በ155 ዓመት እስራት ቀጣ።
የ44፣ 45 እና 71 ዓመት የሆናቸው ሦስቱ ግለሰቦች ባለፈው ጥር የ23 ዓመቱን ወጣት መግላቸውን አምነዋል።
ከወንጀለኞቹ አንዱ የሟች አጎት ነው ተብሏል።
ባለፉት አስር ዓመታት በማላዊ አልቢኖ (ተፈጥሯዊ የቆዳ ቀለማቸው ላይ ችግር የገጠማቸው) ያለባቸው ሰዎች ተዳጋጋሚ ጥቃት እና ግድያ ሲደርስባቸው ቆይቷል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የሰውነት አካላቸው ጥሩ እድል እና ሃብት ያመጣል በሚል ሃሰተኛ እምነት ነው።
አልቢኖ የቆዳ ቀለም በመንጣቱ ምክንያት የሚከሰት ህመም ሲሆን በዘር የሚተላለፍ ነው። አልቢኖ ጥቁር ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ በጣም ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም ሁሉንም የሰው ልጆች ሊያጠቃ ይችላል።
ከቀናት በፊትም ከፍተኛው ፍርድ ቤት አልቢኖ ካለበት ግለስብ ግድያ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የሮማን ካቶሊክ ቄስ፣ የፖሊስ መኮንን እና የህክምና ባለሙያ በሰው አካላት ንግድ ተሳትፈዋል በሚል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ይህም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጣቸው ግለሰቦች ላይ የተሰጠ ውሳኔ ነው ተብሏል።
ውሳኔው እና የረዥም ጊዜ የእስር ቅጣቱ የፍትሕ አካላት በጥቃቶቹ እና በግድያዎቹ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ያሳየ ነው ተብሏል።













