በዋጋ የማይተመነው የሮማ ጥንታዊ ቅርጽ በቴክሳስ ያገለገሉ እቃዎች መሸጫ ሱቅ እንዴት ተገኘ?

የፎቶው ባለመብት, LAURA YOUNG
ላውራ ያንግ በኦስተን፣ ቴክሳስ ወደሚገኝ ያገለገሉ እቃዎች መሸጫ ሱቅ ጉድዊል ጎራ ያለችው እአአ በ2018 ነበር። ወደ ሱቁ ስታመራ ጥሩ እቃ አገኛለሁ ብላ በማሰብ ነው።
እዚያም ገብታ የአንድን ሰው ከደረት በላይ የሰውነት ክፍል የሚያሳይ ቅርጽ ገዛች።
የቅርጹ ዋጋ 35 ዶላር ብቻ ነበር። ገዝታው ከወጣች በኋላም መኪና ውስጥ ወንበር ላይ በቀበቶ አስራ ፎቶግራፍ አነሳችው።
ላውራ ገለልተኛ የሆነች የጥንታዊ እቃዎች ነጋዴ ናት። ለዚህም ነው ቅርጹ ትኩረቷን የሳበው።
ላውራ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ወደ ሱቁ ያመራችው አንዳች ጥሩ እቃ አገኛለሁ ብላ ነበር።
የገዛችውን ቅርጽ ወደ ፀሐይ ብርሃን አውጥታ ስትመለከተውም ጥንታዊ መሰላት።
ከዚያም በፍጥነት ስለቅርጹ መረጃ ለማግኘት ስለሮማ ከእምነ በረድ የተሰራና ከደረት በላይ የሚያሳይ ቅርጽን በጉግል ላይ ፈለገች። ያገኘችው ከያዘችው ቅርጽ ጋር እንደሚመሳሰልም አሰበች።
ላውራ ሌሎች ወደ አዕምሮዋ ተመላለሱ ጥያቄዎችን ከመረመረች በኋላ ቅርጹ ከክርስቶስ ልደት በፊት 2 ሺህ ዓመት ያስቆጠረና ከክርስቶስ ልደት በፊት ወይም ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንደኛው ክፍለ ዘመን የነበረ፤ በዋጋም የማይተመን የሮማ ከደረት በላይ የሚያሳይ ቅርጽ ሆኖ አገኘችው።
በቴክሳስ ሳን አንቶኒዮ የጥበብ ሙዚየም የሚሰሩት ሊንሊ ማክአልፓይን "በጣም ጠቃሚ ታሪክ ያለው እቃ ነው። በገንዘብ እንዴት መተመን እንደሚቻል እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም። ጭራሽ ሊሸጥ የማይገባው እቃ ነው" ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ከደረት በላይ የተሰራው ቅርጹ፣ ከጁሊየስ ቄሳር ጋር የተዋጋውን የሮማውን የጦር መሪ ሴክተስ ፖምፔይን ሊወክል ይችላል።
ሌሎች መረጃዎች ደግሞ የቅርጹ ባለቤት፣ ቅጂ ያልሆኑ የጥበብ ሥራዎችን ከቅጂዎቹ ጋር የሚያስቀምጠውና በጀርመን የሚገኘው የሮማ ቪላ ቅጂ ቅርጽ እንደሆነ አመላክተዋል።
በጀርመን አስቻፈንበርግ፣ ባቫሪያ ከተማ የሚገኘው ፖምፔጃኑም እአአ በ1840ዎቹ የተገነባ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በደረሰበት የቦምብ ጥቃት ክፉኛ ተጎድቷል።
በመሆኑም ቅርጹ ከአስቻፈንበርግ ወደ አሜሪካዋ ኦስተን እንዴት ሊሄድ እንደቻለ ግልጽ አይደለም።
ይሁን እንጂ በወቅቱ የአሜሪካ ወታደሮች ቅርጹን ወደ አሜሪካ ወስደውት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። የአሜሪካ ወታደሮች እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ድረስ በጀርመኗ አስቻፈንበርግ ሰፍረው ቆይተዋል።
በመሆኑም በጦርነት ወቅት የተዘረፈ እቃ ስለነበር ላውራ ቅርጹን እንደ ጥንታዊ እቃ ለመሸጥ አልፈለገችም።
ነገር ግን ቅርጹ ወደ ደቡባዊ የጀርመን ግዛት-ባቫሪያ ከመመለሱ በፊት ለሳን አንቶኒዮ የሥነ ጥበብ ሙዚያም በብድር ለመስጠት ተነጋግራ ነበር።
ይሁን እንጂ ድርድሩ ረዥም ጊዜ የወሰደ በመሆኑ በዚያን ጊዜ ላውራ ቅርጹን መኖሪያ ቤቷ ሳሎን ውስጥ አስቀምጣዋለች።
"በጣም ደስ ይላል። ከሦስት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜም እዚያው ሳሎኔ ውስጥ ተቀምጦ እያየን ነበር" ብላለች።
ቅርጹን ለሳን አንቶኒዮ የሥነ ጥበብ ሙዚየም ማስረከቡ በጣም መራር ጊዜ እንደነበር ላውራ ተናግራለች። ምክንያቱም እንደዚህ በዋጋ የማይተመንና ጥንታዊ እቃ ድጋሚ እንደማታገኝ ታውቃለች።
"ያኔ ከዚህ የተሻለ ጠቃሚ ነገር ባገኝና እርሱን ሸጨው ትርፍ ማግኘት ብችልም እንኳን፣ ቅርጹ አሁንም ለእኔ ምርጡ ነገር ነው " ብላለች።
ላውራ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በሙዚየሙ ውስጥ የተቀመጠውን ቅርጽ ጎብኝታለች። "እዚያ ውስጥ እርሱን በማየቴ ደስ ብሎኛል። ሊቀመጥ የሚገባውም እዚያ ነው" ስትል ተናግራለች።
ቅርጹ በአሁኑ ጊዜ በቴክሳስ በሳን አንቶኒዮ እየታየ ሲሆን እአአ በግንቦት 2023 ወደ ጀርመን ፖምፔጃኑም ሙዚየም ይመለሳል ተብሏል።












