በሳይንስ የበለፀገ የአሳማ ልብ ተገጥሞለት የነበረው ግለሰብ ሕይወቱ አለፈ

የአሳማ ልብ ተገጥሞለት የነበረው

የፎቶው ባለመብት, UNIVERSITY OF MARYLAND SCHOOL OF MEDICINE

በሳይንሳዊ መንገድ የበለፀገ የአሳማ ልብ ቀዶ ጥገና የተደረገለት የዓለማች የመጀመሪያው ግለሰብ የተባለው ሰው ሕይወቱ አለፈ።

ዴቪድ ቤኔት የልብ በሽተኛ ነበር። የአሳማ ልብ ከተገጠመለት በኋላ ለሁለት ወራት ቆይቶ ነው የሞተው።

ግለሰቡ ጤናው መቃወስ የጀመረው ከጥቂት ቀናት በፊት እንደነበር ዶክተሩ ተናግረዋል።

ዴቪድ በዶክተሮች ጥብቅ ክትትል ሲደርግለት ቆይቶ በፈረንጆቹ ማርች 8 ይህችን ዓለም ተሰናብቷል።

ሰውዬው የመጀመሪያው የአሳማ ልብ በቀዶ ጥገና እንዲገጠምለት የፈቀደው ሂደቱ ለሞት ሊዳርገው እንደሚችል በመረዳት ነው።

በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የጤና ማዕከል ያሉ ዶክተሮች ቀዶ ጥገናውን እንዲያደርጉ ከአሜሪካ መንግሥት ሰዎች ፈቃድ አግኝተዋል።

ዴቪድ የሰው ልብ በቀዶ ጥገና ሊገጥምለት ስለማይችል ነው የአሳማ ልብ የሞከረው።

ከቀዶ ጥገናው በፊት ለስድስት ሳምንታት በማሽን እርዳታ ነበር ሲተነፍስ የከረመው።

ታኅሣሥ 29 ቀን ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ዓለም አጀብ ካለ በኋላ የቀሩትን ቀናት ከቤተሰቡና ወዳጆቹ ጋር አሳልፏል።

ነገር ግን እየቆየ ጤናው ይቃወስ መጣ። ዶክተሮቹም ተደናገጡ።

"በጣም ጀግና እና ልዩ የሆነ ሰው ነው። እስከ መጨረሻው ነው የተፋለመው" ይላል የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ባርትሊ ግሪፊዝ።

የሰውዬው ልጅ የሆነው ዴቪድ ጁኒዬር የአባቱ ቀዶ ጥገና ለሌሎች የተስፋ ጭላንጭል እንዲሆን ይመኝ እንደነበር ኤፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ዶክተር ግሪፊዝ ከዚህ ቀደም ቀዶ ጥገናው መሳካቱ የሚለገስ የሰውነት አካል አጥተው ለሚሞቱ ሰዎች ተስፋ ሰጭ ነው ብለው ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ ውጥ የሚለገስ የሰውነት አካል በማጣት በየቀኑ 17 ሰዎች ይሞታል። 100 ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ መጠባበቂያ መዝገብ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።

የአሳማ ልብን ለሰው ልጅ በቀዶ ጥገና መግጠም የሚለው ሐሳብ ለረዥም ጊዜ ጥናት ሲደርግበትና ሲብላላ የቆየ ጉዳይ ነው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ኒው ዮርክ የሚገኙ ዶክተሮች የአሳማ ኩላሊት በተሳካ ሁኔታ ለሰው እንደገጠሙ ተናግረው ነበር።

ምንም እንኳ ያኔ ይህ ቀዶ ጥገና አዲስ ነገር ቢሆንም ቀዶ ጥገና የተደረገለት ግለሰብ አእምሮው መሥራት ያቆመና የመዳን ተስፋው የመነመነ ነበር።

ከዚያ በኋላ የተሰማው የአሳማ ልብ ቀዶ ጥገና በሕክምናው ዘርፍ ትልቁ ዜና ሆኖ ቆይቷል።

የእንስሳትን አካል ለሰው መግጠምን አስቸጋሪ የሚያደርገው "ሃይፐርኪዩት ሪጄክሽን" የተባለ ሂደት ነው። ሰውነታችን ከሌላ ዝርያ አካል ሲገጥምለት ባዕድ ነገር እንደመጣበት አውቆ የተገጠመውን አካል በደቂቃዎች ውስጥ ይገድለዋል።

ነገር ግን ለአሳማው የሰውነት አካል አስር ጊዜ በሳይንሳዊ መንገድ በልፅጎ ሰውነታችን እንዲቀበለው ማድረግ ተችሎ ነበር።

ቢሆንም ይህንን ሰው ላይ ሞክሮ ሰውነት የተለገሰውን አካል ይገድለዋል አይገድለውም የሚለውን መጠባበቅ ለዶክተሮች በጣም አስጨናቂ ሂደር ነበር።

የልብ ቀዶ ጥገናውን ያደረጉት ዶክተሮች ልቡን ከገጠሙ ከአንድ ወር በኋላም ሁሉም ነገር ሰላም መሆኑን ተናግረው ነበር።

ሰውዬው የሞተበት ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።