በኬንያ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ መድኃኒቶችና ኮንዶሞች መጥፋታቸው ተገለጸ

ኮንዶሞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኬንያ ውስጥ 100 ሺህ ዶላር የሚያወጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኮንዶሞች፣ አጎበሮች እና የቲቢ መድኃኒቶች መጥፋታቸው ተገለጸ።

እነዚህ የህክምና መገልገያዎች የጠፉት በኬንያ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ባለሥልጣን ሥር ከሚተዳደረው መጋዘን ነው ተብሏል።

ኤችአይቪን፣ ቲቢን እና ወባን ለመዋጋት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የድጋፍ ተቋም እንዳለው መድኃኒቶቹና የህክምና ቁሳቁሶቹ ከመጋዘኑ ተሰርቀው በጥቁር ገበያ እንዲሁም ለግል መድኃኒት ቤቶች እንደተሸጡ ይታመናል።

ድርጅቱ አክሎም ባለሥልጣኑ የመድኃኒቶቹን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲል ከስሷል። አንዳንድ መድኃኒቶችም ከትክክለኛ ዋጋቸው በአንድ መቶ እጥፍ ተሸጠዋል ብሏል።

ባለሥልጣኑ በቀረበበት ክስ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።

የኬንያ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ባለሥልጣን እአአ በ2022 በኮቪድ 19 የህክምና ቁሳቁስ ግዥ ላይ የተጭበረበረ መረጃ ይፋ ከወጣ በኋላ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የ78 ሚሊየን ዶላር ጨረታ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ላላቸው ግለሰቦች እና የንግድ ድርጅቶች ያለ አግባብ ይሰጥ እንደነበር ተነግሯል።

ይህም ፕሬዚደንት አሁሩ ኬንያታ የባለሥልጣኑን ቦርድ እና ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል።

ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከ1.4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለኬንያ ያዋለው የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ከባለሥልጣኑ በጠፉ መድኃኒቶችና ቁሳቁሶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።