ናሚቢያዊቷ ዶክተር ለህሙማን ባሳየችው ፍቅር ተሸለመች

የፎቶው ባለመብት, Dr Esperance Luvindao/Points of Light
ናሚቢያዊቷ ዶክተር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለህሙማን በነጻ የበይነ መረብ (ኦንላይን) የማማከር አገልግሎት በመስጠቷ ተሸለመች።
ዶክተር ኢስፔራንስ ሉቪንዳ ትባላለች። የ31 ዓመት ወጣት ስትሆን በአቅራቢያቸው የህክምና ተቋማት የማያገኙ ሰዎችን በበጎ ፈቃደኝነት ታማክራለች።
በዚህም እአአ ከ2019 ጀምሮ ከ44 ሺህ በላይ ህሙማንን መድረስ ችላለች።
በዚህ በጎ ተግባሯም የ'ፖይንትስ ኦፍ ላይት' ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።
'ፖይንትስ ኦፍ ላይት' ሽልማት ለማኅበረሰባቸው ለውጥ ለሚተጉ በጎ ፈቃደኞች የሚሰጥ ሽልማት ነው።
ዶ/ር ኢስፔራንስ ይህንን የበጎ ፈቃድ ሥራዋን የጀመረችው ገና ከህክምና ትምህርት ቤት ተመርቃ በሰራችበት ሰሜናዊ ናሚቢያ አካባቢ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚያዩትን ፈተና ከተረዳች በኋላ ነበር።
በርካታ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ለመጓዝ ይገደዳሉ። ይህ ብቻም ሳይሆን የህክምና ተቋም ከደረሱ በኋላ በዶክተር ለመታየት 10 ሰዓት እና ከዚያ በላይ መቆየት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ባሳሰባት ጊዜ ነበር ታዲያ ዶ/ር ኢስፔራንስ በነጻ የኦንላይን የማማከር አገልግሎት መስጠት የጀመረችው።
ከዚህም ባሻገር 'ዋን ስቴፕ አት ኤ ታይም' የሚል እንቅስቃሴ ጀምራ አንገብጋቢ የሆኑ መድኃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን በመግዛትና ወደ ገጠር በመላክ ከ35 ሺህ በላይ ናሚቢያውያንን ረድታለች።
የጀመረችው ይህ እንቅስቃሴ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በተደረገው የክትባት ዘመቻም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ዶ/ር ኢስፔራንስ ስለ ሽልማቱ ተጠይቃ " ደስታየ ወደር የለውም። በመሸለሜ ክብር ተሰምቶኛል። ሁሌም እንደምለው የምንሰራው ለመሸለም አይደለም፤ ነገር ግን የምንወደውን ሥራ በመስራት መሸለም መባረክ ነው" ብላለች።
ዶ/ር ኢስፔራንስ በናሚቢያ ዋና መዲና ዊንድሆክ ሜዲካል ዶክተር ናት።
በተጨማሪም በማኅበረሰብ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ እንዲሁም በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ስለ ህሙማን እንክብካቤ በመናገር ትታወቃለች።












