ቦሪስ በኮቪድ ወቅት ስላዘጋጁት ግብዣ ከእንደራሴዎች ጥያቄ ሊቀርብላቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ነምበር ቴን በሚባለው መሥሪያ ቤታቸው ኮቪድ-19 ባየለበት ወቅት ስላዘጋጁት ድግስ ከሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ ሊቀርብላቸው ነው።
ነባር የእንግሊዝ መንግሥት ባለሥልጣን የሆኑት ሱ ጌሪ፤ ቦሪስ ጆንሰንን የተለመከተ አንድ ሪፖርት ያወጣሉ ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
ነገር ግን ሪፖርቱ ይፋ ከመደረጉ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ከሕዝብ እንደራሴዎች ጋር ፍጥጫ ይጠብቃቸዋል።
ፖሊስ በበኩሉ የራሱን ምርምራ አድርጎ ውጤቱን ማክሰኞ ዕለት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የሜት ፖሊስ ኮሚሽነር ክሬሲዳ ዲክ እንዳሉት የቦሪስ አስተዳደር ኮቪድ-19ን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ በጣለበት ወቅት በተለያዩ የመንግሥት ሕንፃዎች የመጠጥ ድግሶች ነበሩ።
ይህ የፖሊስ የምርመራ ውጤት ለቦሪስ ጆንሰን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።
ዳውንኒንግ ስትሪት በተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና መሥሪያ የሚገኝበት ሥፍራ በኮቪድ-19 ምክንያት ሰዎች ቤታቸው ሳሉ እሳቸው ግን የመጠጥ ድግስ አዘጋጅተዋል የተባሉት ቦሪስ ከሰሞኑ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንጆቹ ግንቦት 20/2020 የመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት አንድ "ሥራ ነክ" ድግስ ተዘጋጅቶ በመገኘቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለው ነበር።
ነገር ግን ሰኔ 2020ም በተመሳሳይ የልደት ድግስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተዘጋጅቶ ነበር የሚሉ ዘገባዎች ብቅ ማለት ጀምረዋል።
አንዳንድ ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴዎች ቦሪስ ከሥልጣን እንዲወርዱ ቢጠይቁም ሚኒስትሮች ደግሞ የሱ ጌሪ ምርመራ ውጤት ይፋ እስኪሆን እንጠብቅ እያሉ ነው።
ወግ አጥባቂው ቶሪ ፓርቲ ምርመራው ይፋ ከተደረገ በኋላ በቦሪስ መንግሥት ላይ እምነት የለንም የሚል ደብዳቤ ሊፅፉ አቅደዋል። ይህ ደግሞ ቀጣዩ የዩኬ መንግሥት ማነው ወደሚል ሽኩቻ ሊያስገባ ይችላል።
ኮመንስ ለተሰኘው የታችኛው ምክር ቤት አባላት መግለጫ የሚሰጡት ቦሪስ የምርመራውን ውጤት እየተጠባበቁ ሲሆን ውጤቱ ለሕዝብ መች ይፋ እንደሚሆን ግን አልታወቀም።
ሌበር ፓርቲ በበኩሉ መንግሥት የሕዝብ እንደራሴዎች የምርመራውን ውጤት አንብበው እንዲያገናዝቡ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
የታችኛው ምክር ቤት አባላት ኃላፊ የሆኑት ጃኮብ ሪስ-ሞግ የአሁኑ የእንደራሴዎችና የቦሪስ ፍጥጫ ከሌላው ጊዜ የተለየ እንደሚሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጃኮብ አክለው የካቢኔው አባላት በሙሉ ቦሪስን የደገፉት "ያልደገፉ ሚኒስትሮች ሥልጣን እንዲለቁ ስለሚገደዱ ነው" ብለዋል።
ትይዩ [ሻዶው] ዋና አቃቤ ሕግ የሆኑት ኤሚሊ ቶርንቤሪ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድግሶቹን በተለመከተ የቀረበባቸውን ወቀሳ ችላ ማለታቸው ትክክል አልነበረም።
ኤሚሊ አክለው ቦሪስ ስለተካፈሏቸው ድግሶች በመዋሸታቸው ምክንያት አሁን ስላለው የኑሮ ውድነትም ሆነ ስለ ሩሲያ ወደ ዩክሬን መገስገስ የመወሰን ሥልጣን የላቸውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከአንድም ሁለት ሶሥት አራቴ በቢሯቸው ድግሶች አዘጋጅተዋል ተብለው መወቀስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የዩናይት ኪንግደም ሕዝብን ያስቆጣው ጉዳይ ጠቅላዩ ድግስ ሲደግሱ ሕዝቡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎበት ቤቱ መከርቸሙ ነው።












