እራሷን ያጠፋችው የ11 ዓመት ታዳጊ እናት ፌስቡክ እና ስናፕቻትን ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዲት እናት ልጃቸው እራሷን ያጠፋችው በማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ እንደሆነ ተናግረው ፌስቡክ እና ስናፕቻትን ከሰሱ።
መጠሪያውን ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ እና ስናፕቻት ልጃቸው ራሷን ለማጥፋቷ ተጠያቂ እንደሆነ እናት ተናግረዋል።
አምና እራሷን ያጠፋችው የ11 ዓመቷ ታዳጊ ሰሊና ሮድሪገዝ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢንፊልድ ነበር የምትኖረው።
ፌስቡክ እና ስናፕቻት ለተጠቃሚዎች ያቀረቡት አደገኛ አሠራር ለታዳጊዋ ሞት ምክንያት ነው በሚል ክስ ተመሥርቷል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አነጋጋሪ ከሆነ ሰነባብቷል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሚወክለው 'ሶሻል ሚዲያ ቪክቲምስ ሎው ሴንተር' በሰሊና እናት ስም ክሱን ከፍቷል።
መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገው ተቋም ባቀረበው ክስ መሠረት፤ ሰሊና ለሕልፈት የተዳረገችው ከመጠን ባለፈ የኢንስታግራም እና ስናፕቻት ሱስ ምክንያት ነው።
እናት ልጃቸው ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳትጠቀም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በተደጋጋሚ ቀምተዋት ነበር። ነገር ግን ደጋግማ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ትመለስ እንደነበር ተናግረዋል።
"ሰሊና በተደጋጋሚ ለሱስ የአእምሮ ሕክምና ተደርጎላታል። እንደ ሰሊና የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ያለበት ሰው እንዳልገጠማቸው ሐኪሟ ተናግረዋል" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
ሰሊና ከመሞቷ በፊት በድባቴ እና እንቅልፍ በማጣት ትሰቃይ ነበር።
በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምታጠፋው ጊዜ ጨምሮ ነበር።
ሰሊና በበይነ መረብ ለወሲባዊ ብዝበዛ ከመጋለጧ ባሻገር ምስሎቿ በክፍል ጓደኞቿ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቀው ነበር።
ይህ ክስተት የአእምሮ ሕመሟን አባብሶታል።
ክስ የተመሠረተባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋሞች፤ ሆነ ብለው ጎጂ ምርትን ለገበያ በማቅረብ ነው ፍርድ ቤት የሚጠየቁት።
"ተከሳሾቹ የፈጠሩት ማኅበራዊ ሚዲያ ልጆችን የሚያማልል ነው። ልጆችን ከሱስ ለመከላከል ምንም ጥንቃቄ አልተደረገም። ማኅበራዊ ሚዲያ ልጆች አእምሮ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ቢያውቁም ቁጥጥር ግን አላደረጉም" ይላል የክስ መዝገቡ።
የስናፕቻት ቃል አቀባይ በሰሊና ሞት ሐዘን እንደተሰማው ለቢቢሲ ቢገልጽም ክሱን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ከአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ጋር ሆኖ ገጹን ጤናማ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጿል።
ፌስቡክ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠም።
ያለፈው ጥቅምት ላይ የቀድሞው የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን፤ ድርጅቱ ልጆችን የሚጎዳ አሠራር እና ይዘት ማቅረቡን አጋልጣ ነበር።
የፌስቡክ መስራችና አለቃ ማርክ ዙከርበርግ በበኩሉ፤ የደኅንነት ጥበቃ እና የአእምሮ ጤና ለድርጅቱ ቀዳሚ ትኩረት ናቸው ብሏል።












