ማያ አንጀሎ በአሜሪካ የስሙኒ ሳንቲም ላይ በማረፍ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ሆነች

አዲሱ የስሙኒ ሳንቲም

የፎቶው ባለመብት, US Treasury

የአሜሪካ ግምጃ ቤት የገጣሚ ማያ አንጀሎ ስም እና ምስልን በተለምዶ ኳርተር (ሩብ) በመባል በሚታወቀው የአሜሪካ የ25 ሳንቲም ላይ ያሳተመ ሲሆን ይህም አንጀሎን የመጀመሪያዋ ስሟ በሳንቲም ላይ የተቀረጸ ጥቁር ሴት አድርጓታል።

ገጣሚ፣ ጸሃፊ እና የመብት ታጋይ አንጀሎ በአሜሪካ ፕሬዘዳንት የበአለ ሲመት ላይ ግጥም በማቅረብ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት በመሆን ታሪክ መስራቷ ይታወሳል።

ከማያ አንጀሎ በተጨማሪም በዚህ የአሜሪካ የኳርተር ፕሮግራም በተባለው እቅድ ውስጥ ሌሎች ፈር ቀዳጅ ሴቶች በሳንቲሞች ላይ ስማቸው ያረፈ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የጠፈር ተመራማሪ፣ የጎሳ መሪ እና ተዋናይ ይገኙበታል።

ይህ አዲስ እቅድም በሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት የግምጃ ቤት ፀሀፊ አድናቆት ተችሮታል።

"ገንዘባችንን በአዲስ መልክ በቀረፅን ቁጥር ስለ ሀገራችን - ዋጋ ስለምንሰጣቸው ነገሮች እንዲሁም እንደ ማህበረሰብ እንዴት እየተሻሻልን እንደመጣን ለመናገር እድሉ አለን" ሲሉ የግምጃ ቤት ጸሃፊዋ ጃኔት የለን ሰኞ እለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ማያ አንጀሎ ደራሲ እና የማሕበራዊ ተሟጋች - እ.ኤ.አ. በ 2014 በ 86 ዓመቷ ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለየችው።

በ1969 በታተመው እና "አይ ኖው ዋይ ዘ ኬጅ በርድ ሲንግስ" በሚለው እና ስለ ግለ ታሪኳ የሚያወራው መጽሃፏን ተክትሎ እውቅናን አትርፋለች።

እንዲሁም በደርዘን የሚቆጠሩ የክብር ዲግሪዎችን የተቀበለችው አንጀሎ ከ30 በላይ ለገበያ የቀረቡ መጽሃፍቶቿን በህይወት ዘመኗ አበርክታለች።

እ.ኤ.አ. በ 2010 በአሜሪካ ከፍተኛው የሲቪል ሽልማት የሆነውን የነፃነት ፕሬዝዳንታዊ ሜዳሊያ በፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ አማካኝነት ተበርክቶላታል።

አዲሱ የስሙኒ ሳንቲም ማያ እጆቿን ዘርግታ የሚያሳይ ምስሏንም ይዟል። ከበስተጀርባዋም የሚበር ወፍ እና የምትወጣ ጸሃይ የሚታዩ ሲሆን ይህም "ግጥሞቿን ብሎም ህይወቷን የኖረችበትን የህይወት መንገድ ተመስርቶ የተቀረጸ ነው" ሲል የአሜሪካ የግምጃ ቤት አስታውቋል።

የ25 ሳንቲሙ የፊት ገጽታ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት የጆርጅ ዋሽንግተን ምስል ይዟል።

ተቋሙ በቀጣዮቹ አራት አመታት ሌሎች አሜሪካዊያን ሴቶችን የያዘ 20 ተጨማሪ የ25 ሳንቲሞችን ለመገበያየነት ለማዋል አቅዷል። በዚህ አመት ለመጀመሪያዋ ሴት አሜሪካዊት ጠፈርተኛ ለሳሊ ራይድ እውቅና ለመስተጥ እንዲቀረጽ ታቅዷል።

ማያ አንጀሎ ከእናቷ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Maya Angelou

እንዲሁም ዊልማ ማንኪለር ለተሰኘችው የቸሮኪብሔር የመጀመሪያዋ ሴት መሪ እና ለነባር የአሜሪካ ነዋሪዎች መብት በመሟገቷ በተመሳሳይ በሳንቲሙ ላይ ትሰፍራለች።

በ20 ብር ኖት ላይ ያረፉትን ፕሬዘዳንት አንድሪው ጃክሰንከምድር በታች ባለ የባቡር መስመር ውስጥ በባርነት የተያዙ ሰዎችን ባዳነው የጥቁሮች መብት ተሟጋች ሃሪየት ቱብማን ለመተካት ሂደቶች መጀመራቸውም ታውቐል።

ታሪክ የሰሩ ሴቶች በአሜሪካ የመገበያያ ገንዘቦች ላይ እምብዛም አይታዩም። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዋ የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ማርታ ዋሽንግተን የ1 ዶላር የብር ሰርተፍኬት ላይ ቦታ አግኝታ የነበረ ሲሆን የአሜሪካዊቷ ጀግና ፖካሆንታስ በ20 ዶላር ኖት ላይ በቡድን ምስል ውስጥ ተካታ ነበር።