በፊልም ቀረፃ ላይ በተከሰተው ግድያ ክሶች ሊመሰረቱ እንደሚችል ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት በኒው ሜክሲኮ በአንድ ፊልም ቀረፃ ላይ በተከሰተው ግድያ የወንጀል ክስ ሊመሰረት ይችላል ሲል የአሜሪካ ፖሊስ አስታወቀ።
ታዋቂው ተዋናይ አሌክ ባልድዊን በቀረፃው ላይ ባዶ መሆን በነበረበት ሽጉጥ የተቀባበለ በመሆኑ ባጋጣሚ በተኮሰው ጥይት የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯን ሃሊና ሁቺንስን በጥይት ሲገድል እና ዳይሬክተሩን ደግሞ አቁስሏል።
መርማሪዎች እንደተናገሩት ሽጉጡ ተቀባብሎ እንደነበር የሚጠቁሙ ፍንጮች እንዳገኙና በደህንነቱም ዙሪያ አንዳንድ ቸልተኝነት ነበር ብለዋል።
የግዛቲቱ አቃቤ ህግ ሜሪ ካርማክ-አልትዊስ ሊመሰረት ስለሚችለው ክስም በተመለከተ "ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ ናቸው" ሁሉም ቢሆኑ ከዚህ ነፃ እንዳልሆኑም ተናግረዋል።
የፖሊስ የመጀመሪያ ግኝቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሳንቴ ፌ ፖሊስ ኃላፊ አዳን ሜንዶዛ በበኩላቸው " በፊልም ቀረፃው ላይ ሌሎች የተቀባበሉ ሽጉጦች እንደነበሩ ጥርጣሬዎች አሉን" ብለዋል።
አክለውም "በፊልም ቀረፃው ላይ የተቀባበሉ ሽጉጦች እንዴት እንደነበሩ ለማወቅ እንሞክራለን። ምክንያቱም በስፍራው መገኘት አልነበረባቸውም" ሲሉም አክለዋል።
ፖሊስ እስካሁን 600 ማስረጃዎችን ማግኘቱን የተናገሩት ኃላፊው ከነዚህም መካከል ሶስት ሽጉጦች እና 500 ጥይቶች ይገኙበታል።
"እውነታው ግልጽ ነው ብዬ አስባለሁ ። የተቀባባለ መሳሪያ ለአሌክስ ባልድዊን ተሰጥቷል። መሳሪያው በሌሎች ፊልሞች ላይ እንዳለው ባዶ ሳይሆን ጥይት ከመኖር በተጨማሪ የተቀባበለ በመሆን ሁቺንስን ሲገድል ዳይሬክተሩን ሱዛን ደግሞ አቁስሎታል" ብለዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ተኩሱ በተከተሰበት ፊልም ቀረፃ ወቅት እስከ 100 የሚደርሱ ሰዎች ነበሩ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊ ሽጉጥ የሆነውን ኮልት 45 ሪቮልቨር ለተዋናዩ ከመሰጠቱ በፊት የፊልሙ መሳሪያ ተቆጣጣሪ ሃና ጉቴሬዝ-ሪድ እና ረዳት ዳይሬክተር ዴቭ ሆልስ ይዘውት እንደነበር ኃላፊው አረጋግጠዋል።












