አሜሪካ ካቡል ውስጥ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ንጹሃን መገደላቸውን አመነች

በጥቃቱ ከተገደሉት ህጻናት ሁለቱ
የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ከተገደሉት ህጻናት ሁለቱ

አሜሪካ በአፍጋኗ ዋና ከተማ ካቡል ሠራዊቷ ጠቅልሎ ከመውጣቱ በፊት በፈጸመችው የሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] ጥቃት 10 ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አመነች።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በጥቃቱ ዙሪያ ባካሄደው ምርመራ አንድ የእርዳታ ሠራተኛና ዘጠኝ የቤተሰቡ አባላት ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ልጆች በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጧል።

ከተገደሉት ንጹሃን መካከል በእድሜ ትንሿ ሱማያ የሁለት ዓመት ህጻን ነበረች።

ይህ የአንድ ቤተሰብ አስር አባላትን የገደለው አሰቃቂ የድሮን ጥቃት የተፈጸመው ታሊባን ወደ ዋና ከተማዋ ተመልሶ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት ግርግር በበዛበት የአየር ማረፊያ ላይ የሽብር ጥቃት ከተፈጸመ ከቀናት በኋላ ነበር።

የድሮን ጥቃቱ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ወርራ ለ20 ዓመታት ከቆየች በኋላ ሠራዊቷ አገሪቱን ለቆ ከመውጣቱ በፊት የተፈጸመ የመጨረሻው ጥቃት እንደሆነ ተነግሯል።

የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም ኢላማ የነበረው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ መኪና በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኘው የእስላማዊ መንግሥት ቅርንጫፍ ከሆነው ከአይኤስ-ኬ ጋር ግንኙነት አለው በማለት ለስምንት ሰዓታት ሲከታተለው መቆየቱን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጄነራል ኬኔት ማኬንዚ ተናግረዋል።

የተደረገው ምርመራ እንዳመለከተው የግለሰቡ መኪና ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አለው ከተባለ ግለሰብ ቤት መታየቱንና እንቅስቃሴውም በካቡል አየር ማረፊያ ላይ ሌላ ጥቃት ለመፈጸም አለ ከተባለ ዕቅድ ጋር መያያዙ ተጨማሪ መረጃ በማመልከቱ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህም ሂደት ውስጥ የቅኝት ሰው አልባው አውሮፕላን በኋላ ላይ የታሸገ ውሃ እንደሆነ የታወቀ፤ ነገር ግን ቀደም ሲል ፈንጂ ነው የተባለ ነገር ወደ መኪናው ሲጫን ተመልክቶ ነው ጥቃቱ የተፈጸመበት ተብሏል።

ጄነራል ማኬንዚ ጥቃቱን "አሰቃቂ ስህተት" በማለት የገለጹት ሲሆን፤ ጨምረውም ጥቃቱን ለመፈጸም ያበቃውን መረጃ በመስጠት በኩል ታሊባን ሚና እንዳልነበረው አረጋግጠዋል።

ዛሚሪ አህማዲ በተባለው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ መኪና ላይ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ከአውሮፕላን ማረፊያው ሦስት ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲቆም ነበር።

በጥቃቱ ከተገደሉት አስር ሰዎች መካከል አንደኛው አህማድ ናስር የተባለውና ለአሜሪካ ሠራዊት በአስተርጓሚነት ሲሰራ የነበረ ግለሰብ ነው። ሌሎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ደግሞ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሰሩና ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ ያገኙ ነበሩ ተብሏል።

በጥቃቱ ሰለባ ዘመዶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከጥቃቱ አንድ ቀን በኋላ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት ማመልከታቸውንና ለመጓዝ ጥሪ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን ባወጡት መግለጫ የጥቃቱ ኢላማ በነበረው አህማዲና በአሸባሪው ቡድን መካከል ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበረ እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።

"በዕለቱም የግለሰቡ እንቅስቃሴ ከነበረን ጥርጣሬ በተቃራኒው ሙሉ ለሙሉ ምንም ጉዳትን የሚያስከትል አልነበረም" በማለት "ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ከዚህ አሰቃቂ ስህተትም ትምህርት ለመውሰድ እንጥራለን" ብለዋል።

ከድሮን ጥቃቱ በኋላ
የምስሉ መግለጫ, ከድሮን ጥቃቱ በኋላ