ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤቱ ያነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ አካባቢዎች የማስወጣቱ ውሳኔ እስካሁን ባለው ግምገማ ትክክለኛ ውሳኔ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ነው።

የዛሬው ስብባው የተጀመረው የምክር ቤቱ አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን ለመግለጽ ለአንድ ደቂቃ ጭብጨባ ካደረጉ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከምጣኔ ሃብት እና ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የትግራይ ቀውስ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ አካባቢዎች ማስወጣቱ ትክክልኛ ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ እንዲደርስ ካስገደዱት ምክንያቶች መካከል ኢኮኖሚያዊ እና የኮቪድ-19 ጫናዎችን መሆናቸውን አብራርተዋል።

ግጭቱን ተከትሎ "የተፈናቀሉ እንዲመለሱ እንፈልጋለን፣ የኮቪድ-19 ጫና አለ፣ አገራዊ ፕሮጄክቶች ማለቅ አለባቸው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ጦሩን ከትግራይ ያስወጣው ጦርነቱን ማስቀጥል ስላልቻለ ነው የሚለው አስተያየት የተሳሳተ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይን ግጭት "10 ወይም 20 ዓመት ውጊያ ማስቀጠል ይቻላል። በኢትዮጵያ የማይቻለው እና ያልተለማመድነው በአምስት ዓመት እድገት ማምጣት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከክልሎች 100 ሺህ ልዩ ኃይል ማውጣት ይቻላል። በጥቂት ወራት ግማሽ ሚሊዮን መተኮስ የሚችል ሚሊሻ ማሰማራት ይቻላል። ግጭቱን ማስቀጠል ይቻላል" በማለት የመንግሥታቸው ፍላጎት ግን ይህ አለመሆኑን አብራርተዋል።

ጦሩ ከትግራይ ስለወጣበት ሁኔታ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጦሩን ከትግራይ አካባቢዎች እንዲወጣ ማድረግ የተጀመረው ከምርጫው 15 ቀናት በፊት መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦሩ በተለያየ ጊዜ ከትግራይ አካባቢ ሲወጣ መቆየቱን ገልዋል። "ብዙ ሰው አላወቀም። ከምርጫው 15 ቀን በፊት ብዙ አውጥተናል። ተንቤን አካባቢ የነበረውን 3ኛው ኃይል ስናስወጣ ተጠራጥሮ ሊሆን ይችላል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጨረሻ ዙር መቀለ ከተማ አካባቢ የነበረው ኃይል እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ "የህወሓት ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋዎችን ደቅነው ነበር" ብለዋል።

የህወሓት አመራሮች ከፍተኛ አቅም ያለው ጦር ለመገንባት ዝግጅት ሲደረጉ መቆየታቸውን "በየሰፍራው ሰዎችን የሚያፈናቅሉ እና የሚያጋጩ ቅጥረኞችን የማስፋት ተግባር በህወሓት ሲከናወን ነበር" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይን ግጭት ለማስቆም ሳይሳኩ የቀሩ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ መንግሥት ወደ ግጭት ለመግባት መገደዱን አስረድተዋል።

የተወሰዱ እርምጃዎች

በግጭቱ ውስጥ ጥፋተኛ የተባሉት ላይ ለማነጣጠር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ተናግረው፤ ውጊያው ከተማ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።

መከላከያ ተልዕኮውን ሥነ-ምግባር በተላበሰ መልኩ ሲፈጽም ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በተልዕኮው ወቅት ጥፋተኛ የተባሉ የጦሩ አባላት ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።

መንግሥት ከግጭቱ በኋላ ትግራይን መልሶ ለመገንባት እና ለተጎጂዎች እርዳታ ለማድረስ ከየትኛውም አካል በላይ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሕይወት መስዋት ሆኗል ያሉ ሲሆን እንደማሳያም፤ የቴሌኮም አገልግሎትን መልሶ ለማቋቋም 30 ሰዎች መገደላቸውን አመልክተዋል።

ከትግራይ ግጭት መንግሥት ምን አተረፈ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከትግራይ ግጭት መንግሥታቸው አሳክቶታል ያሉትን ጉዳዮች ዝርዝረዋል። "ለችግሩ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ለሕግ ቀርበዋል ወይም ዳግም መሰል ተግባር ላይ እንዳሰማሩ ሆነዋል" ብለዋል።

ግጭቱ በተጀመረበት ወቅት ጥቃት ተፈጽሞበት የነበረው ሰሜን ዕዝ ነጻ መውጣቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "ወደ ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና አሥመራ ይተኮስ የነበረው ሚሳኤል ተመልሷል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የትግራዩ ግጭት የአገር መከላከያን ለማጠናከር መልካም እድልን ፈጥሯል ብለዋል።

ምጣኔ ሃብት

ውጪ ኢንቨስትመንት 20 በመቶ አድጓል። ምርጫ በተከናወነበት እና የኮቪድ-19 ጫና በነበረበት ሁኔታ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ የነበረው የባንክ የሂሳብ ደብተር ቁጥር 38.8 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው፤ የብር ኖት ለውጡን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ግን 66.2 ሚሊዮን ሰዎች የባንክ ደብተር አላቸው ብለዋል።

የባንክ ሂሳብ ቁጥር መጨመሩ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረው፤ የገንዘብ ኖት መቀየሩ የካሽ ዝውውር ቀንሶ ገንዘብ በባንክ እንዲዘዋወር ማስቻሉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በተመሳሳይ የባንክ ቅርንጫፍ ቁጥር ስለማደጉም ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበት

"የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት አንድ እና ያው አይደሉም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የዋጋ ግሽበት አምና ከነበረው ዘንደሮ የጨመረው ነው ብለዋል። የምርት ዋጋ ጭምሮ የሸማቹ ገቢ ጭማሪ ከሌለው የኑሮ ውድነት ይከሰታል ሲሉ አስረድተዋል።

ከገቢ በላይ ወጪ መጨምሩ የኑሮ ውድነትን መከሰቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በአጭር ጊዜ ሥራ የኑሮ ውድነት መቀነስ አይቻልም ብለዋል።

የግሸበቱ ምክንያት ምንድነው?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የዋጋ ግሸበቱ ምክንያቶች የዘረዘሩ ሲሆን የመጀመሪያው ምክንያት የአቅርቦ እና ፍላጎት አለመጣጠም መሆኑን አመልክተው፤ ሌላው "ፍላጎት እያደገ ምርት በሚፈለገው ልክ እያደገ አይደለም ካሉ በኋላ ለዋጋ ግሽበት ሁለተኛው ምክንያት በአቅርቦር ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሳንካዎች ናቸው።"

ሦስተኛ የመንግሥት የፊስካል እና የፖሊሲ ቁጥጥር መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አውስተዋል። "ወደ ገበያ የምናስገባው ገንዘብ የዋጋ ግሽበት ጭማሪ እንደማያስከትል ማወቅ አለብን" ብለዋል።

ሌላ አነስተኛ ድርሻ ቢኖረውም አምራቾች የምርት ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ አለማቅረባቸው ሌላኛቸው የዋጋ ግሽበት የሚያስከትል መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ይህን የዋጋ ግሸበት ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን በዝርዝር ተናግረዋል።

እንደ ምሳሌም መንግሥት ነዳጅን በገዛበት ዋጋ ለአገር ውስጥ ገበያ ቢያቀርብ የኑሮ ውድነት ሊያስከትል ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ። በዚም ምክንያት መንግሥት የነዳጅ ዋጋን በመደጎም ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረቡ 47.8 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ

የታላቁን የሕዳሴ ግድብ በማስመለክት ኢትዮጵያ ሰላማዊ የልማት ጉዞ እንዲሆን ትፈልጋለች ብለዋል።

"ሌሎች ይህን እንዲገነዘቡ እንፈልጋለን" ካሉ በኋላ ዛፍ የምንተክለው ኢትዮጵያ ተጠቅማ ሱዳን እና ግብጽ ተጨማሪ ውሃ ማግኘት እንዲችሉ ነው ብለዋል።

"የምንሰፈልገው ሰላም እና እድገት ነው። ለመጨረስ እንተጋለን [ግደቡን] የኢትዮጵያ አምላክ ያግዘናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ዲፕሎማሲ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የማያስፈልጓት በርካታ ኤምባሲዎች እንዳሏት እና ይህም ለአገር ተጨማሪ ወጪ መሆኑን አመልክቷል።

በቀጣይ ዓመት መስከረም ወር ላይ የሚመሰረተው መንግሥት ከ30 በላይ ኤምባሲዎችን እንደሚዘጋ ተናግረዋል።