በሊባኖስ የወደቀ ኢኮኖሚ የተመሰሉት የፋሲካ ብስኩቶች

የሰዎች የምግብ አዘገጃጀትና አለባበስ በአብዛኛው ያላቸውን የኢኮኖሚ ደረጃ ያመላክታል። የግለሰብን ብቻም ሳይሆን የአገር ኢኮኖሚንም ማንፀባረቂያ መስታወት ነው።
ሰው ኑሮውን ይመስላል እንደሚባለው ማለት ነው።
ታዲያ ሊባኖሳውያን በአገራቸው ኢኮኖሚ የተመሰሉ የፋሲካ ብስኩቶችን አዘጋጅተዋል።
በሊባኖስ የፋሲካ በዓልን ለሚያከብሩ የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ባህላዊ ‘ማሞል’ ብስኩት መስራት ወይም መግዛት የተለመደ ነው።
ማሞል የተሰኘው ይህ ብስኩት በውስጡ ቅቤ፣ ለውዝ፣ ፍራፍሬ፣ ሥጋ እየተሞላ የሚዘጋጅ ነው።
ሊባኖሳውያን በዚህ ጣፋጭ ምግብ ይኮራሉ። በፋሲካ በዓል፣ በኢድ አልፈጥር እንዲሁም በኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ከማዕዳቸው የማይታጣ ምግብ ነው።
በሊባኖስ ማሞል ብስኩትን አለማዘጋጀት ማለት በፋሲካ ዶሮ ወጥ፤ በኢድ አልፈጥር ገንፎን እንዳለመስራት ማለት ነው።
ይህ ብስኩት በዓውድ ዓመት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። በዘንድሮው የፋሲካ በዓል ግን ነገሮች ከወትሮው የተለየ ሆነዋል።
ሪታ ስታምቦሊ የግሪክ ኦርቶዶክስ አማኝ ስትሆን ነዋሪነቷ ከቤሩት አንድ ሰዓት ያህል በመኪና በምታስጉዘው ዛህል ነው።
ዘንድሮ እያዘጋጀች ያለችው ሞሞል ከወትሮው ለየት ይላል። ብስኩቱን ለመስራት ያድቦለቦለችው ሊጥ ውስጥ የቴምር ፍሬ እያስገባች ነው ያዘጋጀቸው።
ለወትሮው ሥጋ ነበር የምትጨምርበት።
“አሁን ኢኮኖሚው ወድቋል። ድህነት ውስጥ ነው ያለነው። ጉዟችን ወደ ኋላ ሆኗል። በፊት እንደምንኖረው እየኖርን አይደለም፤ ስጋ የምናገኘው በወር አንድ ጊዜ ነው” ትላለች።
ሪታ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ፀሐፊ ሆና ነው የምትሰራው። የአገሪቷ ኢኮኖሚ መላሸቅ ልክ እንደ ሌሎቹ ሊባኖሳዊያን የደመዋዟን የመግዛት አቅም አሳንሶታል።
“ሁለት ልጆች አሉን። በኪራይ ቤት ነው የምንኖረው። እኔ እና ባለቤቴ እንሰራለን ግን ይህም ሆኖ ገቢያችን በቂ አይደለም” ትላለች።
ምንም እንኳን ብስኩቷ ውስጥ መጨመር የምትወደው ፒስታሽዎ የተባለ ፍሬ ቢሆንም አሁን ግን ይህን ማድረግ አልቻለችም። ፒስታሽዎ እንደ ለውዝ ያለ ጠንካራ ሽፋን ያለው ውድ ፍሬ ነው።
በዚህ ዓመት ግን ይህንን አትሰራም። የምትሰራው የማሞል ብስኩት ቁጥርም ከዚህ ቀደም ከምታደርገው አነስተኛ ነው።
አሁን ብስኩቱ ውስጥ የምትጨምረውን የፒታሽዎ ፍሬ በቅቤ ተክታዋለች። ይህም ቢሆን ግን ዋጋው ቀላል አይደለም።
"ቅቤው የደመወዜን አንድ ሦስተኛ ይወስዳል" ትላለች።

በርካታ ሊባኖሳዊያን የምግብ ባንክ ጠባቂ ሆነዋል። የሶሪያ ስደተኞችን እና ለአደጋ የተጋለጡ ሊባኖሳውያንን የሚደግፈው የልማትና የእርዳታ ድርጅት የሚቀርብለት የእርዳታ ጥያቄ ጨምሯል።
ሁኔታውም በጣማ የተባባሰ ሆኗል። በአገሪቷ ውስጥ ባለው ፖለቲካ እና አለመስማማት እርዳታዎችም ባክነዋል።
እአአ በ2020 መጨረሻ ከኢራቅ የተገኘ የእርዳታ ስንዴ ለተረጂዎች መሰራጨት ሲገባው ስታዲየም ውስጥ አላግባብ መቀመጡ ተነግሯል።
በዚያው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ በቤሩት ወደብ ላይ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ ከሲሪላንካ የተገኘ የሻይ ቅጠል ድጋፍም ለፕሬዚደንቱ ጠባቂዎች ቤተሰቦች ተሰጥቷል።
በአገቷ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን እርምጃ እየወሰዱ ነው። ሂዝቦላህ እና የጦር ድርጅቶች የራሳቸውን የገበያ ማዕከል ከፍተዋል። ነገር ግን በርካሽ የሚሸጡት ለራሳቸው አባላትና ደጋፊዎቻቸው ነው።
ታዲያ በቤሩት ዝነኛው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና 'ሊባነን ፎር ቱሞሮው' በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አምባሳደር የሆነው ጆሴፍ ታውክ ላለፉት ሦስት ቀናት ከቡድኑ ጋር ሆኖ 9 ሺህ የሚሆኑ ማሞል ብስኩቶችን አዘጋጅቷል። ብስኩቶቹን በማዘጋጀት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይሰጣሉ። የመድሃኒትም ድጋፍ ያደርጋሉ።
አገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የአራት ቀናት ቤት ውስጥ የመቀመት ገደብ ጥላለች።
በመሆኑም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የፋሲካ በዓልን ፤ ሙስሊሞችም የኢፍጣር ሥነ ሥርዓትን የሚያከብሩት ቤታቸው ሆነው ያላቸውን ነገር እየተቃመሱ ነው።












