ዩክሬን ውስጥ እዳቸውን መክፈል ያልቻሉ ሰዎች የውስጥ ልብስ ለጨረታ ቀረበ

የውስጥ ልብስ

የፎቶው ባለመብት, Setam.net.ua

ዩክሬን ወስጥ እዳቸውን መክፈል ያልቻሉ ሰዎች የውስጥ ልብስ ጭምር ለጨረታ መቅረቡ በርካቶችን አስገርሟል።

በዩክሬን ማዕከላዊ ከተማ ክሪይቪ ሪህ የተለያዩ አልባሳት እና ጫማዎች በአገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ ለሽያጭ ቀርበዋል።

የአልባሳቱ መነሻ የመሸጫ ዋጋ ደግሞ 70 ሳንቲም ዶላር እንደሆነ ተገልጿል።

መስሪያ ቤቱ ከአልባሳት በተጨማሪ ላሞችና በጎችንም ጭምር ለሽያጭ አቅርቧል። የ

ኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ እስከ 2 ሚሊየን የሚደርሱ ዩክሬናውያን ከመንግሰት አበዳሪ ተቋማት የተለያዩ የብድር አይነቶችን ወስደዋል።

ቢቢሲ ከአንድ ዩክሬን መስሪያ ቤት ባገኘው መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት ብቻ የተበዳሪዎች ቁጥር በ300 ሺ ጨምሯል።

ባለፈው ዓመት በአንድ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ መልዕክት ሁለት የቤት እንስሳ የሆኑ ውሻዎች ለሽያጭ ቀርበው በርካቶች ተቃውሟቸው ን ሲገልጹ ነበር።

አንድ የሕዝብ እንደራሴ ደግሞ እዳዋን መክፈል ያልቻለች አንዲት ጡረተኛ ውሻዎቿን ሸጣም ቢሆን እዳዋን መክፈል አለባት ብለው ነበር። በወቅቱም በርካቶች ተቃውሟቸውን ገልጸው ነበር።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዴኒስ ማሊዩስካ ወደኋላ ላይ ግን የቤት እንሳስቱን መሸጥ እምብዛም አዋጪ ነገር እንዳልሆነና ቢቻል በጥሩ ገንዘብ ሊሸጡ የሚችሉ ንብረቶች ላይ ትኩረት ቢደረግ ይሻላል ብለዋል።

ኦኢሲዲ የተባለው አንድ ተቋም ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት መሰረት የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ዩክሬን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያጋጥማት የሚችል ሲሆን ይህም ባለፉት 10 ኣመታት ከታየው በጣም ትልቁ ነው።

ወረርሽኙን ተከትሎም አገሪቱ ካላት 41 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 9 ሚሊዮን የሚሆኑት እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ ይኖራሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰራው ጥናት መሰረት ደግሞ ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ከአጠቃላይ ህዝቡ 40 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የቤተሰብ አባላቸው ስራ አጥቷል።

ዩክሬን ውስጥ እዳቸውን መክፈል ያልቻሉ ሰዎችን ንብረት ለሽያጭ የሚያቀርበው ድረ ገጽ የተቋቋመው በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር። የፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚለው እስካሁን 506 ሚሊየን ዶላር ከሽያጩ ተገኝቷል።

ከዘህ በተጨማሪም መስሪያ ቤቱ እዳቸውን መክፈል ካልቻሉ ሰዎች የተወሰዱ ንብረቶችን ለወላጅ አልባ ህጻናት፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች በነጻ እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተገልጿል።