በሩሲያዊው አሌክሴ መታሰር ምክንያት የ11 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ሊቋረጥ ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያና አውሮፓን የሚያስተሳስረው ንግድ በዋዛ የሚታይ አይደለም። አውሮፓ 40 ከመቶ ጋዝ የምታገኘው ከሩሲያ ነው።
አሁን ደግሞ እጅግ ግዙፉ የጋዝ ማስተላለፍያ ቧንቧ ከሩሲያዋ ኪንጊሴፐን እስከ ግራስዋልድ ጀርመን ድረስ የሚዘረጋ ነው።
ይህ ፕሮጀክት በርካታ አገራትን የሚያቋርጥና በባልቲክ ባህር ስምጥ ተቀብሮ የሚያልፍ ውስብስብ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ ጀርመንን የሩሲያ የኢኮኖሚ እስረኛ ሊያደርጋት ይችላል የሚለው ስጋት ገና ከፕሮጀክቱ መጠንሰስ ጀምሮ ሲነገር የነበረ ነው።
አሁን ደግሞ ጀርመንና ሩሲያ በአሌክሴ ናቫልንሊ ጉዳይ እየተነታረኩ ነው የሚገኙት።
በርካታ አገራት ጀርመን በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንደትጥል እየገፏፏት ይገኛሉ።
በተለይም ከሩሲያ እስከ ጀርመን እየተዘረጋ ያለውን ዘመናዊ የጋዝ ማስተላለፍያ ቧንቧ ሥራ እንዲቋረጥ እንድታደርግ ነው በዋናነት ግፊቱ እየበረታ ያለው።
"ኖርድ ስትሪም 2" የሚል ስም የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት በአውሮፓ እጅግ ግዙፍ ከሆኑት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው።
በአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባላት፣ አባል አገራት በሩሲያ ላይ ማናቸውን ዓይነት ማዕቀብ በመጣል ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ አድርገዋል።
አሌክሴ ናቫልኒ በሩሲያ ከተመረዘ በኋላ በጀርመን ሕክምና አድርጎ ወደ አገሩ ሲመለስ በፕሬዚዳንት ፑቲን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ እስር ቤት መወሰዱ አይዘነጋም።
አሜሪካ በዚህ የጋዝ ማስተላለፍያ ቧንቧ ፕሮጀክት ላይ ቀደም ብላ ማዕቀብ ጥላለች።
ማዕቀቡ የተጣለው ቧንቧዎቹን እየቀበረ ባለው የሩሲያ ግዙፍ መርከብ ላይ ነው።
አሜሪካ በተደጋጋሚ እንደምትለው ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ሩሲያ በአውሮፓ ላይ የሚኖራትን ተጽእኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀብ የጣለባት የሩሲያ መርከብ ፎርቹና የምትባለዋ ስትሆን ይህ ማዕቀብ የተጣለው ትራምፕ ሥልጣን ሊለቁ በነበሩባቸው የመጨረሻ ቀናት ነው።
ሆኖም ይህን ማዕቀብ ጆ ባይደንም የሚደግፉት እንጂ የሚቀለብሱት አይሆንም ተብሏል።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ስምምነት ለአውሮፓ መጥፎ ስምምነት ነው ሲሉም ነበር።
በቅርቡ ሥልጣን የሚለቁት የጀመርኗ መራሂት መንግሥት አንጌላ መርከል በማዕቀቡ ጉዳይ ተጠይቀው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ፕሮጀክቱ ሩሲያ ለጀርመን የምትልከውን የጋዝ መጠን በእጥፍ እንደሚጨምር እጅግ ቁልፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ሆኖም መንግሥታቸው ጉዳዩን ከባይደን አስተዳደር ጋር እንደሚመክርበት ተናግረዋል።
ይህን የጋዝ ማስተላለፍያ ቧንቧ 2ሺህ 460 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 94 ከመቶ ተጠናቋል።
ሥራው በ2019 መጨረሻ ላይ ለአንድ ዓመት የቆመው በአሜሪካ ማዕቀብ የተነሳ ነበር።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ዋናው የቧንቧዎቹን መቅበር ሥራ የሚሰራው ኩባንያ ሥራውን ለማቆም ተገዶ ነበር።
ባለፈው ወር ግን ፎርቹና መርከብ በጀርመን የውሀ አካል ሥር የመቅበሩን ሥራ ጨርሳ በዴንማርክ ውስጥ ሥራውን ለመቀጠል በዝጅግጀት ላየዕ ነበረች። ሆኖም ማዕቀቡ ሥራውን እንዲቆም አስደርጓታል።
አሁን ፎርቹና መርከብ በባልቲክ ባህር ላይ ነው የምትገኘው።
የ44 ዓመቱ የፑቲን ተቺ አሌክሴ ናቫልኒ ኖቪቾክ በሚባል የነርቭ መርዝ ከተመረዘ በኋላ ሕይወቱ በተአምር የተረፈችው የጀርመን ሐኪሞች ባደረጉለት ርብርብ ነው።
ሆኖም ማገገሙን ተከትሎ ወደ እናት አገሩ ሩሲያ በድፍረት ለመመለስ መወሰኑ ብዙዎችን አስደንቋል።
በርካታ ጋዜጠኞች እሱ በተሳፈረባት አውሮፕላን አብረውት ወደ ሩሲያ የተጓዙ ሲሆን እንደተፈራውም ከበርሊን ሩሲያ እንደገባ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የሱን መታሰር ተከትሎ በርካታ አገራት ቁጣቸውን በሩሲያ ላይ ሰንዝረዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ የአሌክሴ መታሰር በጀርመንና በሩሲያ መካከል ችግር የሚፈጥር ነው ካሉ በኋላ በዚህ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት ላይም የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
በዚህ ሳምንት ሃይኮ ማስ ወደ ዋሺንግተን ተጉዘው አቻቸውን አንቶኒ ብሊንከንን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።












