ትኩስ ምግብ አቅራቢው የዶሮ ሥጋ የሚያሞቅ 'ጌም' ሠራ

ጌም ኮንሶል

የፎቶው ባለመብት, KFC

ኬኤፍሲ የተባለው ታዋቂው ትኩስ ምግብ አቅራቢ ድርጅት የዶሮ ሥጋ የሚያሞቅ 'ጌም ኮንሶል' መሥራቱን ይፋ አድርጓል።

"መጫወቻው ውስጡ ማሞቂያ ስላለው ተጫዋቾች በፈለጉት ሰዓት አውጥተው ሊመገቡት ይችላሉ" ብሏል ኬኤፍሲ።

ጌም ኮንሶል ማለት በውስጥ የተለያዩ የቪድዮ ጌሞችን ያዘለ ማጫወቻ ነው።

ኩባንያው እንዳለው ቴክኖሎጂው የተሠራው በዓለም አቀፍ የጌም አምራች ድርጅት ነው።

ማሞቂያ አዘሉ የጌም ማጫወቻ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ዓይነት ጨዋታ እንደያዘ ነው ትኩስ ምግብ አቅራቢው ድርጅት የሚናገረው።

ኬኤፍሲ ባለፈው ሰኔ ይህንን ቴክኖሎጂ ለገበያ እንደሚያቀርብ ሲናገር በርካቶች ይህ ተራ የማስታወቂያ ሥራ ነው ሲሉ አጣጥለውት ነበር።

ድርጅቱ ግን ይህንን እውን አድርጊያለሁ ብሏል።

ትንሹ ማሽን በውስጡ የዶሮ ሥጋና ሌሎችም ዓይነት ምግቦች ማመቂያ እንዲገጠምለት የሆነው የበይነ መረብ ጌም ተጫዋቾች ትኩስ ምግብ አዘው እንዳይቀዘቅዝባቸው 'በማሰብ' ነው።

ማሽኑ ልክ እንደ ሲዲ አሊያም ዲቪዲ ማጫወቻ ሊታሰብ ይችላል።

ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ዓይነት ጌም አስገብተው ሊጫወቱበት ይችላሉ።

"በዚያ ላይ ምግብዎን አሙቆ ይጠብቅዎታል. . . እና ምን ጎደለ?" ይላሉ የኬኤፍሲ ቃል አቀባይ ማርክ ቺቨርስ ለቢቢሲ ሲናገሩ።

"ሶኒ ወይም ማይክሮሶፍት የቪዲዮ ጌሞችን ሲያመርቱ እንዴት አድርገን ነው የዶሮ ስጋ ማሞቂያ የምንገጥምለት ብለው ከተጨነቁ እኛን ሊያማክሩን ይችላሉ።"

ትኩስ ምግብ አቅራቢው ድርጅት ይህንን ቴክኖሎጂ መቼ ለገበያ እንደሚያቀርብ አልታወቀም።

የማሽኑ የዋጋ ተመንም ገና ይፋ አልተደረገም።

ድርጅቱ ባለፈው ሰኔ 'ተራ ማስታወቂያ' ተብሎ የተተቸበትን ዘመቻ ሲጀምር ቢያንስ 11 ሚሊዮን ሰዎች በትዊተር ገፁ የተለቀቀውን ቅንጭብ ማስታወቂያ ተመልክተውታል።

ነገር ግን ኬኤፍሲ እና ኩለር ማስተር ተባብረው አይነኬ የሚመስለውን እውን አድርገናል ብለዋል።

ድርጅቶቹ ይህንን ማሽን ለማበልፀግ በርካታ ውጣ ውረዶች እንዳለፉ ተናግረዋል።

'ጣት የሚያስቆረጥም' በሚለው የማስታወቂያ መለያው የሚታወቀው ኬኤፍሲ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 'ጣት የሚያስቆረጥም' የተሰኘችውን ሃረግ ለጊዜው ለመሻር ተገዷል።