የአልጀዚራ ጋዜጠኞች አይፎን ስልክ በእስራኤል ሰራሽ 'ስፓይዌር' ተጠልፎ እንደነበረ ተደረሰበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ስልክ በአንድ እስራኤል ሰራሽ ስፓይዌር ተቦርብሩ መረጃ ሲጠለፍ እንደነበር አንድ ጥናት አመለከተ።
መረጃ ጠላፊውን ስፓይዌር የሰራው ኤንኤስኦ (NSO Group) የእስራኤል ኩባንያ እንደነበር ተመላክቷል።
ስልካቸው ተጠልፎ ሲበረበርባቸው የነበሩት የአልጀዚራ እውቅ ጋዜጠኞች ብዛት 36 መሆኑም ተደርሶበታል።
ከጋዜጠኞቹ መካከል የሚዲያ ሥራ አስፈጻሚዎችና የዜና አቅራቢዎች ይገኙበታል።
ብርበራውን የደረሰበት ሲቲዝን ላብ የተሰኘ የካናዳ ድርጅት ነው። ይህ የጠለፋ ምርመራ ውጤት ዝርዝር በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ታትሟል።
ዝርዝር ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው የስልክ ብርበራው አይፎን ስልኮች ላይ በሚጫን መተግበሪያ በኩል የተቀነባበረ እንደነበረ ያትታል።
የእስራኤሉ ኤንኤስኦ ግሩፕ ክሱን ያስተባበለ ሲሆን ይህ ሪፖርት እኛ ጠለፋ ስለማድረጋችን በቂ መረጃ የለውም ብሏል።
ሲቲዝንስ ላብ ተመራማሪዎች ግን በማያሻማ ሁኔታ ብርበራውን ደርሰንበታል ይላሉ። ጠለፋውን ካደረጉት ሰዎች ሁለቱ ደግሞ በሳኡዲና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥታት ይደገፉ ነበር ብሏል።
ሲቲዝንስ ላብ እንደሚለው ለጠለፋ የዋለው ሰፓይዌር "ኪስሜት" ተብሎ የሚጠራው ነው። እንደ ዝርዝር ማብራሪያው ከሆነ ኪስሜት ዚሮዴይ ጥቃት ተብለው ከሚጠቀሱ ብርበራዎች ይመደባል። ይህም ማለት የስልኩ አምራች አፕል ኩባንያ ስለ ጉዳዩ ማወቅ እንዳይችል የሚጋርድ ነው።
ይህ ስፓይዌር በአፕል የሶፍትዌር ማሳለጫ (iOS 13.5.1) እና ከአፕል11 ስልኮች ላይ እንዲሰራ የተዘጋጀ ነበር። በወቅቱ አፕል 11 ሞዴል ስልኮች የመጨረሻዎቹ ዘመነኛ ስልኮች ነበሩ።
የካናዳው ሲቲዝን ላብ መጀመርያ ይህን ምርመራ እንዲያደርግ ያስቻለው አልሚሻል የተባለ የአልጀዚራ የምርመራ ጋዜጠኛ ስልኩ ላይ አንዳች ጥርጣሬ ማሳየቱን ተከትሎ ሪፖርት በማድረጉ ነበር።
አልሚሻል ስልኬ ከሩቅ እየተበረበረ ሳይሆን አይቀርም በሚል ወደ ሲቲዝን ላብ ሪፖርት በማድረጉ የሌሎች ጋዜጠኞችም አይፎኖች ሲፈተሹ መረጃቸውን ወደ 3ኛ አካል እየተሻገረ እንደነበር ተደርሶበታል።
ይህ የሆነው በሐምሌ 2020 አካባቢ ነበር።
ኤንኤስኦ የእስራኤል ኩባንያ ክሱን ያጣጣለ ሲሆን እንዲህ አይነት ሥራ የሚሰራው መንግሥታት አደገኛ ሽብር ይደርስብናል ብለው በሚሰጉበት ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት እንጂ ጋዜጠኞችንና ስልካቸውን እንደማይሰልል አብራርቷል።
ድርጅቱ ጨምሮ ባወጣው መግለጫ ዓለምን የተሻለችና ከሽብር የጸዳች ለማድረግ አሁንም በርትተን እንሰራለን ብሏል።
በአልጀዚራ ጋዜጠኞች የቀረበበትን ክስ መሰረት ቢስ ብሎታል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ዙርያ አልጀዚራ የለንደን ቢሮን እንዲሁም የሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት ኢምሬትስ ኤምባሲዎችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።












