ሊባኖስ፡ ለመሠረታዊ ሸቀጦች የሚደረገው ድጎማ እንዳይነሳ ቤይሩት ውስጥ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ መንግሥት ያደርገው የነበረው ድጎማ ሊቀነስ መሆኑን በመቃወም በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት ውስጥ ተቃዋሚዎች መንገዶችን መዝጋታቸው ተነገረ።
የድጎማውን መቀነስ በተመለከተ የወጡ መረጃዎችን ተከትሎ እርምጃውን የተቃወሙ ሰልፈኞች በማዕከላዊ ቤይሩት መንገዶች ላይ ጎማዎችን ያቃጠሉ ሲሆን አንዳንዶቹም ቁጣቸውን ለመግለጽ ወደ አገሪቱ ፓርላማ ህንጻ አምርተዋል ተብሏል።
የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ኃላፊ መንግሥት በዱቄት፣ በነዳጅና በመድኃኒቶች ላይ ያደርግ የነበረው ድጎማ ከቀጣዮቹ ሁለት ወራት በኋላ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ተናግረው ነበር።
በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት ሳቢያ በተለይ ድሃ ቤተሰቦች ላይ ከባድ ማኅበራዊ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት አስጠንቅቀዋል።
ከሰኞ ጀምሮ የሌባኖስ ዜጎች በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ መንግሥት ያደርግ የነበረው ድጎማ ለማንሳት ማሰቡን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ከሰኞ ጀምሮ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።
ሊባኖስ ለተራዘመ ጊዜ እያሰቃያት ባለው የምጣኔ ሐብት ቀውስ ምክንያት የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በመዳከሙ ማዕከላዊው ባንክ ዱቄትና ነዳጅን የመሳሰሉ ምርቶች ከውጭ ለሚያስገቡ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ በቅናሽ እያቀረበ ቆይቷል።
የምጣኔ ሐብት ቀውሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳዊያንን ወደ ድህነት የከተተ ሲሆን፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ቀውሱን የበለጠ አባብሶታል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በቤይሩት ወደብ ላይ ተከስቶ ከ200 በላይ ሰዎችን የገደለውና በሺዎች ያቆሰለውን ከባድ ፍንዳታ ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ያሉትን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጥሰው ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ለፍንዳታው ምክንያት የሆነውን ወደቡ ውስጥ በሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተከማችቶ የነበረውን ሁለት ሺህ ቶን የሚደርስ የአሙኒየም ናይትሬት አደገኛ ንጥረ ነገር እንዳይፈነዳና ጉዳት እንዳያደርስ ባለስልጣናት ለማድረግ አልቻሉም በሚል በወቅቱ በርካታ የሊባኖስ ዜጎች ቁጣቸውን ገልጸው ነበር።
በደረሰው ከባድ ጉዳትና በተቀሰቀሰው ከባድ ተቃውሞ ምክንያት አገሪቱን ያስተዳድር የነበረው የሊባኖስ መንግሥት ስልጣኑን እንዲለቅ ተገዶ ነበር።
















