አሜሪካ፡ በአሪዞና ሾፌር አልባ ታክሲዎች ሥራ ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, WAYMO
በአሜሪካ፣ አሪዞና ግዛት ዋና ከተማ ፊኒክስ ነዋሪዎች በስልካቸው መተግበርያ የሚጠሯቸው ታክሲዎች ተሳዳቢ ሾፌር፣ መልስ የሚያረሳሳ ረዳት የላቸውም፡፡
በቃ መኪናው ውስጥ ማንም የለም፡፡ መሪው አለ፤ ሾፌሩ የለም፡፡ የሚሳፈሩት ሰው አልባ ባዶ መኪና ውስጥ ነው፡፡
ይህ ከጥቂት ዐሥርታት በፊት የሳይንስ ፊክሽን የሚመስል ሐሳብ ነበር፡፡ አሁን ዕውን ሆኗል፤ ወይም እየሆነ ነው፡፡
አሁን መተግበርያውን በስልክዎ በመጫን ሰው አልባ ታክሲ ጠርተው ተሳፍረው የፈለጉበት መሄድ ይችላሉ፡፡
እንደ ራይድ፣ ኡበር፣ ፈረስና ታክሲዬ አገልግሎቶች ማለት ነው፡፡
ልዩነቱ በነዚህ የዌይሞ ታክሲዎች ሾፌር አለመኖሩ ነው፡፡
የጉግል እህት ኩባንያ ዌይሞ ልዩ ደንበኞች ላይ ከዚህ ቀደም ለተወሰነ ጊዜ ይሄ አገልግሎት ሲሞከርባቸው ነበር፡፡
ይህም ኮሮና ከመምጣቱ በፊት ነበር የሆነው፡፡ አሁን የዌይሞ ደንበኞችና ቤተሰቦቻቸው ከሚቀጥሉት ሳምንታት በኋላ ሾፌር አልባ ታክሲ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡
ይህ አገልግሎት ይጀመራል ከተባለበት ሁለት ዓመት ዘግይቶ ነው አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው፡፡
መኪናዎቹ ሾፌር ባይኖራቸውም ከርቀት በተገጠመላቸው መቆጣጠርያ ክትትል ስለሚደረግላቸው ለደኅንበት አስጊ አይደሉም ተብሏል፡፡
አካባቢያቸውን በፍጥነት በካሜራና በራዳር ተመልክተው ውሳኔ የሚሰጡ ሮቦት ታክሲዎች ከአደጋ የራቁ ናቸው ተብሏል፡፡
የትራፊም መብራትን አክብረው፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ሰጥተው ‹30 የሆነው በምክንያት ነው› እያሉ በሰላምና በጤና ተሳፋሪዎቻቸውን ያደርሳሉ፡፡
ለምሳሌ ያልተጠበቀ መንገድ በአደጋ ምክንያት ቢዘጋ ተለዋጭ መንገድ የሚያመቻቹ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው ናቸው፡፡ ሞገደኛ ሾፌር ከፊት ለፊት ቢያጋጥማቸውም ፍሬን አፍነው ይዘው ማሳለፍ ይችላሉ፡፡
ይህን የሚወስኑትም በሰከንድ ልዩነት ነው፡፡እነዚህ ታክሲዎች ለገዜው 130 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ከባቢን የሚሸፍኑ ናቸው፡፡
በፊኒክስና አካባቢዋ በተለይም ቻንድለር፣ ቴምፕ እና ሜሳ አካባቢዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዌይሞ ኩባንያ ደንበኞቹ እስከዛሬ ስለታገሱት አመስግኗል፡፡
በሾፌር አልባ ታክሲዎች አገልግሎት ደንበኞቹ እንደሚረኩም ተስፋ አድርጓል፡፡ዌይሞ 600 ታክሲዎች አሉት፡፡ ሆኖም ምን ያህሎቹን በአሪዞና እንደሚያሰማራ አልገለጸም፡፡
በፊኒክስ ከተማ ከወረርሽኙ በፊት ይሰጡ ከነበሩ የታክሲ አገልግሎቶች እስከ 10እጅ የሚሆኑት ሾፌር አልባ አገልግሎቶች ነበሩ፡፡
ሾፌር አልባ ታክሲዎች በተለይ በወረርሽኝ ዘመን ከሰው ቅርርብን ስለሚያስወግዱ ተመራጭ ይሆናሉ ተብሎ ታስቧል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ሾፌር አልባ ታክሲዎችን መተማመን ጀምረዋል፡፡ ቀጣዩ የኩባንያው እቅድ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ማስፋፋት ይሆናል፡፡
ጉጉል እንደ ቴስላ ሁሉ ላለፉት ዐሥር ዓመታት በሾፌር አልባ መኪኖች ዙርያ አዲስ ነገር ይዞ ለመምጣት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚህም ሲል ራሱን የቻለና ሾፌር አልባ መኪናዎችን የሚያቀርብ ኩባንያን ዌይሞን የመሰረተው፡፡












