ከአሜሪካና ከቻይና ቢሊየነሮች በሀብት ማን ይበልጣል?

የምድራችን ዋነኛ ባለሃብት የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምድራችን ዋነኛ ባለሃብት የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ

የዓለም ሕዝብ መከራውን እየበላ ነው። የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ሚሊዮኖች ሳይሆኑ ቢሊዮኖች ናቸው። ቢሊየነሮች ግን ሀብታቸው ሰማይ እየነካ በተድላ 'እየተሰቃዩ' ነው።

በሀብት የሚያዋኙት የዓለም ቢሊየነሮች በቁጥር ከዓለም ሕዝብ ጋር ሲነጻጸሩ ጥቂቶች ናቸው። በጣም ጥቂቶች። ኧረ በጣም በጣም ጥቂቶች።

ተዝቆ የማያልቅ አዱኛን ካካበቱት መካከል የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ይገኝበታል።

ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ የቢሊየነሮች ሀብት በአማካይ በ27.5 ከመቶ ተመንድጓል። ወይም ደግሞ የ10.2 ትሪሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፤ ይህም ከመጋቢት ወር ወዲህ ብቻ መሆኑ ነው።

መረጃውን ያወጣው የስዊዘርላንዱ ዩቢኤስ ባንክ ነው።

የቢሊየኖች ብዛት ከኮሮናቫይረስ በፊት ቀድሞም ቢሆን ከዓመት ዓመት ጭማሪ እያሳየ ነው የመጣው።

በ2017 ዓ.ም በዓለም ያሉ ቢሊየነሮች በድምሩ ቁጥራቸው 2 ሺህ 158 ነበር። አሁን ስንት ደረሱ?

በድምሩ 2 ሺህ 189 ደርሰዋል። በሦስት ዓመት ውስጥ የቢሊየነሮቹ ቁጥር በ31 ከፍ ብሏል። በጣም ብዙ ነው።

ባንኩ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በዚህ ዓመት የሃብት በረከት ከዘነበላቸው ቢሊየነሮች ዋንኞቹ ኢንደስትሪያሊስቶች ናቸው።

በሦስት ወር ብቻ ሀብታቸው በ44 ከመቶ አድጓል።

ቀጥለው የሚገኙት የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ናቸው።

የተሰማሩበት መስክ የኮቪድ-19 ክስተትን ለመጠቀም የተስማማ በመሆኑ ሀብታቸው 41 ከመቶ ጨምሯል።

ይህ ዘርፍ የሚያቀርበው የአብዛኛው አገልግሎት ፍላጎት ኮቪድ-19 አመጣሽ ነው። ሰዎች በአካል መገናኘት አደጋ እንደሆነ ሲረዱ ወደ በይነ መረብ ዞረዋል። ይህም ለቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ተጨማሪ ቢሊየኖችን ይዞላቸው መጥቷል።

ከጤና ጋር በተያያዙ ምርቶች ላይ የተመሰረቱት ቢሊየነሮችም ኮቪድ-19ን ወደውታል። የሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም የመድኃኒት አምራች ቢሊየነሮች ንግድ ጦፎልናል ብለዋል።

ቁጥር አንድ የፕላኔቷ ቢሊየነር የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ እና የቴስላ ኩባንያ መሥራች ኤሎን መስክ የኩባንያዎቻቸው የአክሲዮን ዋጋ ሰማይ በመንካቱ ሀብታቸው ላይ በላይ እየተከመረ ነው ብሏል ባንኩ።

የቻይና ቢሊየነሮች

ባለፉት 11 ዓመታት የቻይና ቢሊየነሮች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

ሀብታቸው የሚጨምርበት ፍጥነትም አስደንጋጭ ነው። በድምሩ የቻይና ቢሊየነሮች ሀብት በ1 ሺ 146 በመቶ ጨምሯል። ይህም በፈረንጆች ከ2009 ጀምሮ ሲታይ ነው፤ እንደ ባንኩ መረጃ።

ለምሳሌ የታላቋ ብሪታኒያ ቢሊየነሮችን ከቻይና ቢሊየነሮች ጋር ብናነጻጽር የእንግሊዞቹ ቢሊየነሮች ሀብታቸው የጨመረው 168 በመቶ ብቻ ነው።

ያም ሆኖ በቢሊየነሮች ክምችት አሜሪካንን የሚያህል የለም። ቻይናና አሜሪካንን ብናነጻጽር ለምሳሌ አሜሪካዊ ቢሊየነሮች በድምሩ 3.5 ትሪሊዮን ዶላር ሲያካብቱ ቻይናዎች ግን በድምሩ 1.7 ትሪሊዮን ዶላር ሀብት ነው ያፈሩት።

ሆኖም የቻይና ቢሊየነሮች አመጣጥ ለአሜሪካ አስፈሪ ይመስላል። በአጭር ጊዜ እየተቃረቡ ነው።

የታላቋ ብሪታኒያ ቢሊየነሮች ሀብት ተለቅ ያለ ካልኩሌተር ፈልገን ብንደምረው 205 ቢሊየን ዶላር ቢሆን ነው። የጀርመኖች 595 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። የፈረንሳይ ቢሊየነሮች ድምር ሀብት ደግሞ 443 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው።

ስለዚህ ቻይናና አሜሪካ ከአውሮፓዊያኑ ቢሊየነሮች ጋር ሲነጻጸሩ 'ምን ብልተው ነው የሚያድሩት?' ያስብላል።

ማን ለጋስ ነው?

ዩቢኤስ ባንክ እንደሚለው ብዙ ቢሊየነሮች ከኮቪድ-19 በኋላ ደግ፣ ቸር፣ እና ለጋስ ሆነዋል።

"በእኛ ጥናት መሰረት 209 የዓለም ቢሊየነሮች በይፋ ተናግረው የለገሱት ብር ድምር 7.2 ቢሊየነር ዶላር ነው" ይላል ባንኩ። ይህ አሐዝ ከመጋቢት እስከ ሰኔ 2020 ብቻ ቃል ተገብቶ የተለገሰ ነው።

የዚህ ልግስና ባህሪ ከስከዛሬው የሚለየው በፍጥነት መሆኑና ተለጋሽ ተቋማትም ገንዘቡን ለፈለጉት አገልግሎት በፈለጉት መንገድ እንዲያውሉት መደረጉ ነው ይላል ባንኩ።

ጥናቱ የታላቋ ብሪታኒያ ቢሊየነሮች ከብዙ አገሮች አንጻር ትንሹን ልግስና ማሳየታቸው አስገርሞል።

በአሜሪካ ለምሳሌ 98 ቢሊየነሮች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ለግሰዋል። በቻይና 12 ቢሊየነሮች 679 ሚሊዮን ዶላር ልግሰዋል። በታላቋ ብሪታኒያ ግን 9 ቢሊየነሮች ብቻ ናቸው መለገስ የቻሉት። ድምሩም 300 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ ነው።