ፌስቡክ፡ ድርጅቱ ተጠቃሚዎቹ አውስትራሊያ ውስጥ ዜና እንዳያጋሩ እንደሚያግድ ዛተ

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, NIALL CARSON/PA WIRE

ፌስቡክ አውስትራሊያ ውስጥ ተጠቃሚዎቹ ዜና እንዳያጋሩ እንደሚያግድ ዛተ። አውስትራሊያ ውስጥ ፌስቡክ ለዜና እንዲከፍል የሚያስገድድ ሕግ መረቀቁን ተከትሎ ነው ፌስቡክ ይህን ያለው።

የአውስትራሊያ ሕግ አውጪዎች፤ ፌስቡክ፣ ጉግል እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ተቋሞች ለዜና እንዲከፍሉ ይፈልጋሉ።

ጉግል ባለፈው ወር እንዳለው፤ ሕጉ ተጠቃሚዎች መረጃ የሚያገኙበትን ፍጥነት ያጓትታል።

ፌስቡክ ዜና ማጋራትን ላግድ እችላለሁ ማለቱ በአውስትራሊያ ሕግ አውጪዎችና በቴክኖሎጂ ተቋሞቹ መካከል ያለውን ውጥረት አካሮታል።

ሕጉ ከተተገበረ አውስትራሊያዊ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ዜና ማጋራት አይችሉም።

በአውስትራሊያ የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቀው ተቋም አሳታሚዎችና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች እኩል መወዳደሪያ መድረክ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

ፌስቡክ ዜና ማጋራትን አግዳለሁ ማለቱ “ጊዜውን ያልጠበቀና የተሳሳተ” ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ሮን ሲምስ “ሕጉ ፌስቡክ እና ጉግል ከአወስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ፍትሐዊና ግልጽ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።

የፌስቡክ የአውስትራሊያ እና የኒው ዚላንድ ኃላፊ ዊል ኤስተን በበኩላቸው “ሕጉ የኢንተርኔት ባህሪ ያልተገነዘበና መንግሥት እጠብቃቸዋለሁ የሚላቸውን ሚዲያዎች የሚጎዳ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

አሳታሚዎች ወደ ገጻቸው ሰዎችን ለመጋበዝ ፌስቡክን በፈቃዳቸው እየተጠቀሙ፤ ፌስቡክ ግን ለዜና እንዲከፍል የሚያስገድድ ሕግ መሆኑንም አክለዋል።

የአውስትራሊያ ዜና ተቋሞች በፌስቡክ አማካይነት 2.3 ቢሊዮን ጊዜ ዜናቸው እንደታየና ይህም 200 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር እንደሚገመት ኃላፊው አስረድተዋል።

ፌስቡክን የሚጠቀሙ ጓደኛሞችና ቤተሰቦች እንዲጎዱ ስለማይፈልጉም “ዜና ማገድ የመጨረሻ አማራጫችን ነው” ብለዋል።

አንዳንድ ባለሙያዎች፤ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ለዜና መክፈል እንዳለባቸው ያምናሉ።

በስዊዘርላንድ የንግድ ትምህርት ቤት የሚሠሩት ማይክል ዌድ ባለፈው ወር ለቢቢሲ እንዳሉት፤ ጉግል እና ፌስቡክ ለረዥም ጊዜ በነፃ ሲገለገሉ ቆይተዋል።

ጉግል እና ፌስቡክ ለዜና ገንዘብ የሚከፍሉባቸው ሁኔታዎች አሉ። በሌሎች አገሮችም ይህን አሠራር የመተግበር እቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።