ኒውዮርክ ታይምስና መሰል ታላላቅ የዜና ምንጮች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲከፍሉ እየተፋለሙ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በበይነ መረብ ያሉ የዜና ድረገፆች ችግር ላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ኑሮ ከበደን ብለው ከገበያ ወጥተዋል፡፡ችግሩ የተፈጠረው ሰዎች በበይነመረቡ ዓለም ይዘቶቻቸውን በነጻ ማግኘታቸው ነው፡፡
ብዙ የተለፋባቸው የዜና ዘገባዎች ሰልባጅ ሆነዋል፡፡አሁን አዲስ ዘመቻ ጀምረዋል፤ አሳታሚዎች፡፡ ይከፈለን የሚል፡፡ እነ ጉጉል፣ እነ አፕልና እነ ፌስቡክ ቢሊዮን ዶላሮችን በትርፍ ሲዝቁ የዜና ድረገፆች ግን እየኮሰመኑ መሆኑ ፍትሐዊ አይደለም የሚሉ እንቅስቃዎች እዛም እዚም ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡
ጋዜጣና መጽሔት አሳታሚዎች ለነ ጉገል አጭር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ክፈሉን!ጉግልና ፌስቡክ ከዚህ በፊት ለተመረጡ ይዘቶች ክፍያ እንፈጽማለን ብለው ነበር፡፡ ይህንንም በተወሰነ ደረጃ ጀምረውታል፡፡ ይሁንና አታሚዎች እንደሚሉት ገቢው የልብ አያደርስም፡፡የዓለም ግዙፉ ጋዜጣ ኒውዮርክ ታይምስ አፕል ኩባንያ ትርፌን እየወሰደብኝ ነው ሲል ቅሬታ አቅርቧል፡፡
የአውስትራሊያ ጋዜጦችም ተመሳሳይ ጥያቄ ከማንሳት አልፈው ክስ ለመመስረት እየተዘጋጁ ነው፡፡አፕል ጋዜጦቹ በመተግበሪያ ቋቱ (አፕል ስቶር) በኩል ሲሸጡ ከእያንዳንዱ ሽያጭ 30 በመቶ ትርፍ ይወስዳል፡፡
ቢያንስ ይህን እንዲተው ወይም የትርፍ ህዳጉን እንዲቀንስ ነው አሳታሚዎቹ እየጠየቁ ያሉት፡፡በዚህ ሳምንት መጀመርያ ጉግል ከአውስራሊያ አሳታሚዎች ጋር ጠብ ውስጥ ገብቷል፡፡ አሳታሚዎቹ የሚሉት ጉግል የሚከፍለን ብር በጭራሽ የልብ አያደርስም፣ ይጨመር ነው፡፡
የበይነመረቡን ዓለም የተቆጣጠሩት አፕል፣ ጉጉልና ፌስቡክ ለአሳታሚዎች አጥጋቢ ክፍያ ለመፈጸም ዳተኛ ሆነዋል፡፡የአሜሪካ ግዙፎቹን ጋዜጦች ማለትም ኒውዮርክ ታይምስን፣ ዋሺንግተን ፖስትን እና ዎልስትሪት ጆርናልን በገበያና ንግድ ጉዳዮች የሚወክለው ዲጂታል ኮንቴንት ኔክስት የተባለው ኩባንያ ለአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ የቅሬታ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡
ቅሬታው አፕል ለምን ከትርፋችን 30 ከመቶ ይወስድብናል የሚል ነው፡፡ የአይፎን ስልኮች አምራቹ አፕል በመተግበሪያ ቋቱ (አፕ ስቶር) እነዚህ ጋዜጦች ሲሸጡ ከትርፋቸው ከ15 እስከ 30 ከመቶ ኮሚሽን ይበላል፡፡
ነገር ግን አማዞን ‹አንዳንድ ደንቦችና ግዴታዎችን ስለሚያሟላ› የዚህን ያህል የትርፍ ኮሚሽን አይወሰድበትም፡፡አሁን አሳታሚዎቹ እያሉት ያሉት አማዞን የሚያሟላቸውና እኛ የማናሟላው ደንብና ግዴታዎች ምንድን ናቸው፤ ይገለጽልን ነው፡፡
አፕል ከአሳታሚዎች ብቻ ሳይሆን ከጌም አምራቾችም ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል፡፡ኤፒክ ጌምስ በዓለም የዝነኛው ፎንትናይት ቪዲዮ ጌም አምራች ነው፡፡ ይህ ጌም ከአፕል ስቶር ሲገዛ አፕል የትርፉን 30 ከመቶ ይወስድበታል፡፡
ይህ ያበሳጨው ኤፒክ ጌምስ ኩባንያ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ በአውስትራሊያ የሸማቾች ውድድር ኮሚሽን አዲስ ሕግ አርቅቋል፡፡ ሕጉ እነ ጉግልና ፌስቡክ እንዲሁም ጉግል ፕሌይ ከገጾቻቸው በኩል ለሚለጥፏቸው ማናቸውም የጋዜጣና መጽሔት ይዘቶች ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚጠይቅ ነው፡፡
ጉግል በበኩሉ አሁን ከፍ ያለ የይዘት ጥራት ያላቸው ጋዜጦችና መጽሔቶችን ገንዘብ መክፈል ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡ የአውስትራሊያ የገበያ ቁጥጥር ባለሥልጣን ‹‹አሳታሚዎች የሚከፈላቸውን ዋጋ መደራደር እንዲችሉ የመጫወቻ ሜዳው ፍትሐዊ እንዲሆን ጠይቋል፡፡
የቢዝነስ አዋቂዎች እንደሚገምቱት እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች በበይነ መረብ ለታየ ነገር ሁሉ ክፍያ ሊፈጽሙ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ሙያዊ ከፍታው ደርዝ ያለው፣ በጥራትና በትጋት የተሰራ የዜና ዘገባ ክፍያ ሊታሰብለት ይገባል ባይ ናቸው፡፡‹‹ርካሽ ነገር ርከሽ ነው፡፡ የትም በነጻ ሊገኝ ይችላል፡፡
ሙያውን የጠበቀና ብዙ የተለፋበትን ይዘት ግን እንደ መናኛ ነገር በበይነ መረብ ለጥፎ ምንም አለመክፈል በምንም መመዘና ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ይዘቶች በገንዘብ ካልተደገፉ ይጠፋሉ፡፡›› ይላሉ በስዊዘርላንድና በሲንጋፖር ቢዝነስ ትምህርት ቤቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ዋዴ፡፡
‹‹ጉግል፣ ፌስቡክና ሌሎች የጋዜጦችን ምርት እየቦጨቁ በነጻ ሲዘሮት ኖረዋል፣ ለረዥም ጊዜ፤ ይህ ነገር ሊያበቃ ይገባል ብለዋል ፐሮፌሰሩ ለቢቢሲ፡፡ ጉግል በበኩሉ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ የፈቃድና የአከፋፈል ፕሮግራም ለማውጣት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ ከፍ ላሉ የጋዜጣ ሥራዎች ክፍያ መፈጸም ይጀምል ብሏል፡፡
ይህ የክፍያ ፕሮግራም በዚህ ዓመት መጨረሻ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የጉግል ቃል አቀባይ ‹‹ሰዎች ግልብ መረጃዎች እንዳይነዷቸው፣ ጠለቅ ያለና ውስብስ ዜናዎችን ማግኘት አለባቸው፣ የሚያነቃ፣ የጠራ መረጃን ለሚሰጥ ነገር መጋለጥ አለባቸው፤ ይህ እንዲሆን አሳታሚዎች ገንዘብ ሊያገኙ ይገባል፡፡
ስለዚህ መክፈል እንጀምለን›› ብለዋል፡፡ዶ/ር ሪጫርድ ስሚዝ እንዲህ ይላሉ፡፡‹‹ጉጉልን የሚያኖረው አሳታሚው የፈጠረው መረጃኮ ነው፡፡ስለዚህ መረጃ ፈጣሪው ከሌለ ጉግል ራሱ የለም፡፡ ለራሱ ህልውና ሲል ትርፉን ማጋራት ይኖርበታል››












