ትራምፕ ቪዛና ግሪን ካርድ ለጊዜው እንዳይሰጥ አገዱ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ እስከ 2020 መጨረሻ ለውጭ አገር ሰዎች ቪዛና ግሪን ካርድ እንዳይታተም መመሪያ አስተላለፉ።

ይህ መመሪያ ተግባራዊ ሲደረግ በቴክኖሎጂና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ስልጠና ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች፣ ከግብርና ውጭ ባሉ ዘርፎች የጉልበት ሠራተኞች፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞች እንዲሁም የከፍተኛ ኩባንያ ሥራ አስኪያጆችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ቪዛ ለማግኘት ይቸገራሉ።

ዋይት ሐውስ እንደሚለው እርምጃው የተወሰደው በወረርሽኙ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት የደረሰባቸው አሜሪካዊያን ሥራ እንደልብ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው።

የዶናልድ ትራምፕ ተቺዎች በተቃራኒው እርምጃው ኮሮናቫይረስን አስታኮ የውጭ ዜጎችን ማግለል ነው ይላሉ።

አዲሱ የቪዛ ሕግ ማንን ይመለከታል?

ይህን አዲስ ደንብ በተመለከተ በተሰጠ መግለጫ እንደተገለጸው በዚህ የቪዛና የግሪን ካርድ ክልከላ በትንሹ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ችግር ውስጥ ይገባሉ።

ከእነዚህ ውስጥ 170 ሺህ የሚሆኑት ቋሚ የመኖርያ ፍቃድ (ግሪን ካርድ) ለማግኘት ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው። ዋይት ሐውስ ባለፈው መጋቢት ቋሚ የመኖርያ ፍቃድ ጥያቄ መቀበልን ለጊዜው እንዳቆመ ገልጾ ነበር። ነገር ግን ያ ጊዜያዊ እቀባው ሰኞ ዕለት እንደሚያበቃ ይጠበቅ ነበር።

አሁን በዚህ መመሪያ እንደ አዲስ እንደተራዘመ መረዳት ይቻላል።

አሁን የአሜሪካ ቪዛ የተመታላቸው ሰዎች ግን ይህ መመሪያ አይመለከታቸውም ተብሏል።

ይህ አዲሱ መመሪያ ኤች ዋን ቢ ቪዛ (H-1B visas) የያዙ ሰዎችንም አጉል የሚያደርግ ነው። ብዙውን ጊዜ በዚህ የቪዛ ዓይነት ተጠቃሚዎች ከሕንድ የሚመጡና በኮምፒውተርና ቴክኖሎጂ የሰለጠኑ ናቸው።

ይህ ቪዛ ሲሊከን ቫሊ በሚባለው አካባቢ በረቀቁ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሥራዎችን ለአሜሪካዊያን በውድ ክፍያ ከሚሰጡ በርካሽ ዋጋ ለውጭ አገር ሠራተኞች በተለይም ለሕንድ ወጣቶች እንዲሰጡ ሲያስችላቸው ነበር።

በዚህ የቪዛ ዓይነት ብቻ ወደ አሜሪካ ሥራ አግኝቶ ለመግባት ባለፈው ዓመት ብቻ 225,000 ሰዎች ያመለከቱ ሲሆን 85,000 የሚሆኑት ቪዛው ተመቶላቸዋል።

ይህ መመሪያ ኤች ቱቢ (H-2B) ቪዛ አመልካቾችንም ይመለከታቸዋል። በዚህ ቪዛ ብዙውን ጊዜ ወደ አሜሪካ የሚገቡት በሆቴልና ቱሪዝም በአጠቃላይ መስተንግዶ ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው።

ነገር ግን በእርሻ፣ በምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪና በጤና ዘርፎች ባሉ ሥራዎች ውስጥ ለመሰማራት የሚመጡት አዲሱ መመሪያ አይመለከታቸውም ተብሏል።

ይህ የትራምፕ መመሪያ ጄዋን (J-1) የቪዛ አመልካቾችንም የሚያግድ ነው። የጄዋን የቪዛ አመልካቾች ብዙውን ጊዜ የአሜሪካ ቆይታ እንዲራዘምላቸው የሚፈልጉ የቤት ሠራተኞች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው። በዚህ እገዳ ውስጥ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮችና ተመራማሪዎች አልተካተቱም።

ከዚህ በተጨማሪ ትልልቅ ኮርፖሬሽኖችን በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩ ሰዎች የሚጠይቁት ኤል ቪዛም ቢሆን እግድ ተጥሎበታል። ይህ የትራምፕ እርምጃ ሙገሳንም ትችትንም እያስተናገደ ይገኛል።

የትራምፕ ደጋፊዎች እርምጃው ቅድሚያ ለአሜሪካዊያን የሚለውን የትራምፕን ፍልስፍና የተከተለና ተገቢ ነው ሲሉ ተቺዎች ግን ሰውየው ለስደተኞች ያላቸውን ጥላቻ ወረርሽኙን አስታከው በተግባር እያዋሉት ነው ይላሉ።

የዶናልድ ትራምፕ የቪዛና የግሪን ካርድ ክልከላን ተከትሎ በርካታ የአሜሪካ ኮርፖሬሽኖች መመሪያው ሥራችንን ይጎዳዋል በሚል ተቃውመውታል። አዲሱን መመሪያ ከተቃወሙት ውስጥ የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ይገኝበታል።