ካንሰር፡ 14 ሴ.ሜትር የሚረዝም 'ቀንድ' ከአንድ ግለሰብ ጀርባ ላይ ተወገደ

ከካንሰር ታማሚ ላይ የተወገደው ቀንድ

የፎቶው ባለመብት, BMJ Case Reports

የምስሉ መግለጫ, ካንሰሩ አድጎ ይህን መሳይ ቅርፅ የያዘው በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው

በእንግሊዝ አንድ የካንሰር ታማሚ 5 ኢንች (14 ሴንቲ ሜትር) የቀንድ ቅርፅ ያለው ባዕድ አካል ከጀርባው ላይ በሕክምና ተወገደለት።

የእንግሊዝ የሕክምና ጆርናል በሪፖርቱ እንዳስቀመጠው የ50 ዓመቱ ግለሰብ፤ በካውንተስ ቸስተር ሆስፒታል ከጭኑ ላይ ሥጋ በመውሰድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል።

የጆርናሉ ፀሐፊዎች ሕመሙ ግለሰቡን እምብዛም ለከፋ ጉዳት የሚዳርገው ያልነበረ ሲሆን፤ ለፀሐይ ብርሃን መጋለጥ ግን የለበትም ብለዋል። የጉልበት ሠራተኛ የሆነው ግለሰቡ፤ የቤተሰቦቹ የጤና ታሪክ የቆዳ ካንሰር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ያሳያል።

ቀንድ መሳዩ ካንሰር እድገቱ የጨመረው በሦስት ዓመታት ውስጥ ነው። ይሁን እንጅ በሰውነቱ ውስጥ የሚገኙ የሊንፍ እጢዎች ጤናማ እድገት ያላቸው መሆኑ ሐኪሞቹን አስገርሟል።

የሪፖርቱ ፀሐፊዎች አጋታ ማርታ ፕሎንክዛክ፣ ራሚይ አሊይ፣ ህሪስኬሳ ሻርማ እና አንካ ብሬህና እንዳሉት፤ ስለ ቆዳ በሽታ ግንዛቤ እያስጨበጡ ነበር።

"እንደዚህ ዓይነት በጣም በግልፅ የሚታይ፣ ትልቅ 'ስኳሞስ ሴል ካርሲኖማ' የተሰኘው፤ ነፃ የህክምና አገልግሎት የማግኘት እድል ባላቸው እና በአደጉ አገራት በሚኖር ታማሚ ችላ የተባለው የቆዳ ካንሰር ዓይነት አልፎ አልፎ የሚገጥመን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም አሁን ባለው የቆዳ ካንሰር ግንዛቤና ሕክምናው ቢኖርም፤ አፈትልከው የሚወጡ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

አክለውም ግለሰቡ ያጋጠመው የካንሰር ህመም በሁለተኛ ደረጃነት በጣም የተለመደው ዓይነት የቆዳ ካንሰር ሲሆን፤ የድራጎን ቀንድ ዓይነት መልክ ከመያዙ በፊት በሚደረግ የህክምና ክትትል በቀላሉ መዳን ይችል ነበር ብለዋል።