ስለ ኢቦላ ቫይረስ በማስተማር የሚታወቀው ጋዜጠኛ ተገደለ

ኢቦላን ሲዋጋ የነበረው ጋዜጠኛ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ስለ ኢቦላ ቫይረስ ትምህርት በመስጠት የሚታወቀው የኮንጎ ጋዜጠኛ በመኖሪያ ቤቱ ተገድሎ ተገኝቷል።

የአገሪቱ ጦር እንዳሳወቀው ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች የጋዜጠኛው ቤት ገብተው ገድለውታል፣ ሚስቱ ላይም ጉዳት አድርሰው፣ መኖሪያ ቤቱን ደግሞ በእሳት አቃጥለው አምልጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ በታሪኳ አይታ የማታውቀው የኢቦላ ቫይረስ አደጋ ተጋርጦባታል። ሆኖም ኢቦላን ለመመከት ወዲያ ወዲህ የሚሉ ሰዎች አደጋ ሲደርስባቸው ይስተዋላል።

በተለይ ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። አልፎም የጤና ተቋማት የጥቃት ዒላማ ሲሆኑ ይታያሉ።

ቫይረሱ እውነት አይደለም ብለው የሚያምኑ በርካታ ዜጎች መኖራቸው ለጥቃቱ ምክንያት ይሆናል እየተባለ ነው። ሐኪሞች ሕብረተሰቡ በቫይረሱ ምክንያት ባህላዊ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን እንዲተው ቢወተውቱም ሰሚ አላገኙም።

ጋዜጠኛ ፓፒ ሙምቤሬ ማሃምባም የዚህ ገፈት ቀማሽ ሳይሆን አልቀረም እየተባለ ነው። ጋዜጠኛው በተገደለበት ወቅት ቤቱ ውስጥ ባለው የማህበረሰብ ራድዮ ስለቫይረሱ አስከፊነት እየሰበከ ነበር ተብሏል።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ኢቦላ ቫይረስ ብሔራዊ አደጋ ነው ስትል ያወጀችው ባለፈው ዓመት ነበር። ከዚያ ወዲህ 2ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ፤ 3ሺህ ገደማ ደግሞ ቫይረሱ እንዳለባቸው አረጋግጫለሁ ይላል የዓለም የጤና ድርጅት።

ባለፈው ሐምሌ የዓለም የጤና ድርጅት ኮንጎን እያመሳት ያለው ኢቦላ የዓለምን ቀልብ የሚሻ ነው ሲል በይፋ ማወጁ አይዘነጋም።